የ104 ዓመቷ አዛውንት በድብደባ ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 22/2010)

የ104 ዓመት አዛውንት ሴት በእስር ቤት በድብደባ ተገደሉ።

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በሚገኝ እስር ቤት ባለፈው ረቡዕ የታሰሩት ወ/ሮ አምባሮ ሺክህ ዳይብ በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው አልፎ ዛሬ አስከሬናቸው ለቤተሰብ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

የእሳቸው ልጅ የ83 ዓመቱ አዛውንት አሊ አብዱላሂ ፊሂዬም በእስር ቤት የሚገኙ ሲሆን ህይወታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ ህዝቡ እንዲከታተል ጥሪ ቀርቧል።

መነሻው የፖለቲካ አቋም ነው። የአዛውንቷ የልጅ ልጅ የሶማሌ ክልልንም ሆነ የፌደራሉ መንግስትን በመቃወም የተለያዩ ጽሁፎችን በማህበራዊ መድረኮች በማቅረብ የሚታወቅ ነው።

ነዋሪነቱ በእንግሊዝ ለንደን የሆነው የልጅ ልጅ የሚጽፋቸውን እንዲያቆም በተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ቢላክበትም ሊያቆም አልቻለም።

የሶማሌ ክልል ህዝብ ፍጹም በሆነ ጭቆና ውስጥ የሚገኝ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ በውጭ የሚኖሩ የመንግስት ተቃዋሚዎች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የተነሳ በሀገር ቤት በሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ላይ ከእስር ጀምሮ እስከ ግድያ የሚደርስ ርምጃ ይወሰዳል ያሉት የሶማሌ ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ ሊቀመንበር አቶ ጀማል ዲሪዬ የ104 ዓመቷን በማስታወስ ችግር የሚሰቃዩ አዛውንትም የዚሁ ሰላባ ሆነው ተደብደበው መገደላቸውን ይገልጻሉ።

ወ/ሮ አምባሮ ዳይብ በገጠማቸው የመርሳት ችግር /አልዛይመር/ የልጅ ልጅ እንዳላቸው እንኳን ማስታወስ ሳይችሉ በልጅ ልጃቸው ፖለቲካዊ አቋም ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው መገደላቸው በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ዜጎች በምን ዓይነት የጭካኔ አስተዳደር ስር እንደሚገኙ ለዓለም ያሳየ ነው ተብሏል።

ቤተሰብ ዋጋ እየከፈለ ባለበት በዚሁ ኢሰብዓዊ ርምጃ የወ/ሮ አምባሮ ልጅ የ83 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ አሊ አብዱላሂ ከመስጊድ ተይዘው ወደ ማሰቃያ እስርቤት የተወሰዱ ሲሆን ድብደባ እየተፈጸመባቸው በመሆኑ የእሳቸውም ህይወት አደጋ ውስጥ ወድቋል ሲሉ አቶ ጀማል ገልጸዋል።

አስቸኳይ ጫና ካልተደረገ በቀር በቀጣይ ቀናት የእኚህም አዛውንት ህይወት ማለፉ የማይቀር ነው ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹት አቶ ጀማል ለንደን ያለው ልጃቸው ጋር ስልክ በመደወል እንዲያስቆሙት ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ለሰብዓዊ መብትና ለዲሞክራሲ መስፈን በተለያዩ መልኩ የሚንቀሳቀሱ የሶማሌ ተወላጆችን ለማስቆም በክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዘመቻ የተከፈተ ሲሆን በዋናነት ያነጣጠረውም በሀገር ቤት በሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በሶማሌ ክልል ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ግድያ ከዓለም ተደብቋል የሚሉት አቶ ጀማል እንዲህ አይነቱ የጭካኔ ርምጃ አዲስ እንዳልሆነ በመጥቀስ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 68 ሰዎች በሙሉ እስር ቤት ገብተው እየተሰቃዩ ያሉበትን ርምጃም ያስታውሳሉ።

የ104 ዓመቷ አዛውንት በፖሊስ ድብደባ በእስር ቤት የመገደላቸው ዜና ኢትዮጵያውያንን አሳዝኗል።

ጉዳዩን በተለመከተ የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንዲያውቁት የተደረገ ሲሆን አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የ83 ዓመቱ የሟች ልጅ የአቶ አሊ አብዱላሂን ህይወት ለማትረፍ እንዲቻል ህዝቡ ጫና እንዲፈጥር የሶማሌ ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ ጥሪ አድርጓል።