በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አታሼ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ትዕዛዝ ተላለፈ

(ኢሳት ዜና– ሕዳር 22/2010)

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አታሼ ሰክረው በፈጠሩት ችግር ምክንያት ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ዲፕሎማቱ ተስፋኪሮስ ሃይሉ ገብረማርያም ባለፈው ቅዳሜ በስካር መንፈስ መኪና ሲያሽከረክሩ ካደረሱት ተደራራቢ የትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ሲያስቆማቸው ለህጉ ከመገዛት ይልቅ በኢትዮጵያና በቱርክ መሃል ጦርነት እጭራለሁ ሲሉ ማስፈራራታቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።

የቱርክ መገናኛ ብዙሃንም ዲፕሎማቱ ያሳዩትን ያልተገባ ባህሪ መሳለቂያ አድርገውታል።

ይህን ተከትሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ዲፕሎማቱ በአስቸኳይ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ጉዳያቸውን የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙም ታውቋል።

ዲፕሎማቱ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም ሌላ ቅጣት ይጠብቃቸዋል መባሉን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።