(ኢሳት ዜና–ሕዳር 21/2010)በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ ተካሄደ።
በምስራቅ ሀረርጌ ሰሞኑን የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን የህወሃት መንግስት ከስልጣን ይውረድ የሚለው ደግሞ ጥያቄያቸው ነው ።
በወለጋ የተለያዩ ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው።
በሌላ በኩል በአርባምንጭ ከተማ የሚገኘውን አየር ማረፊያ ሲጠብቁ የነበሩ ወታደሮች መጥፋታቸው ታወቋል።
ባህርዳር የሚገኘው የምዕራብ እዝ አየር ምድብ አባላትም ለሁለት ቀናት አድማ አድርገዋል።
ዳግም የተቀሰቀሰውንና ለበርካታ ሰዎች መገደል ምክንያት የሆነውን በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ የተነሳው ተቃውሞ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
በጉርሱም ሁለት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት የህወሃትን መንግስት ያወገዘ ሲሆን በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድም መጠየቁ ተመልክቷል።
ትናንት በጉርሱም በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ አንድ ፖሊስ፣ ሁለት የልዩ ሃይል አባላት ፣ ሁለት ሚሊሺያዎችና አንድ ሲቪል በአጋዚና ፌደራል ፖሊሶች መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ዛሬ ጉርሱም ላይ ህዝቡ ዳውን ዳውን ወያኔ እያለ ቁጣውን ሲገልጽ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች በመኪና ጡሩምባ ድምጽ ሲያጅቡ እንደነበርም ከቪዲዮ ከተገኘ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በቁልቢም ተመሳሳይ ተቃውሞ ተካሂዶ ህዝቡ ግልጽ መልዕክት ለስርዓቱ ማስተላለፉ ታውቋል።
በቦረና ዞን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት ጭምር የተደረገውን ግድያ ህዝቡ እየተቃወመው ሲሆን ዛሬ በዲሎ የህዝብ ንቅናቄ መደረጉ ተሰምቷል።
በተያያዘ ዜናም ትላንት ምሽት በመከላከያ ተሽከርካሪ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ወደ ትግራይ ሊጓጓዝ የተጫነ ስኳር አዳማ ላይ በህዝብ ተቃውሞ መታገቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩል በአርባምንጭ ባለፈው ማክሰኞ ከምሽቱ 5 ሰዓት ሲሆን በከተማዋ የሚገኘውን አየር መንገድ ሲጠብቁ የነበሩ 16 የመከላከያ ሰራዊት አባላት እስከነ ሙሉ ትጥቃቸው መጥፋታቸውን ከኢሳት የመረጃ ምንጮች ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የወታደሮቹን መጥፋት ተከትሎ በከተማዋ ውጥረት መስፈኑም ታዉቋል።
በመጀመሪያ 13 ወታደሮች ሲጠፉ፣ 3 ወታደሮች ደግሞ የጠፉትን ፈልገን እናመጣለን ብለው በመውጣት በዚያው መጥፋታቸውንና ሁሉም ወታደሮች የት እንደገቡ የታወቀ ነገር አለመኖሩ ተመልክቷል።
በተያያዘ ዜናም ባህርዳር የሚገኘው የምዕራብ ዕዝ አየር ምድብ አባላት ለሁለት ቀናት አድማ ማድረጋቸው ታውቋል።
ከ15 በላይ የሚሆኑት ወታደሮች ትምህርት እንድንማር ቃል የተገባልን ተግባራዊ አልሆነም በሚል አድማ ያደረጉ ሲሆን፣ ወታደራዊ ደንብ አስከባሪዎች በመክበብ ከክፍላቸው እንዲወጡ እንዳደረጓቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ማክሰኞና ረቡዕ የተካሄደው አድማ ዛሬ ስለመቀጠሉ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።