(ኢሳት ዜና–ሕዳር 20/201)የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ማዕከላዊ ኮሚቴ በመቀሌ ሲያካሂድ በቆየው ስብሰባ ከፍተኛ ግምገማ ያደረገውና ርምጃ የወሰደው በዋናነት በትግራይ ክልል በሃላፊነት ላይ በሚገኙ አመራሮች ላይ መሆኑን ለስርአቱ ቅርበት ያላቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
አቶ አባይ ወልዱ ከፓርቲው ሊቀመንበርነትና ስራ አስፈጻሚነት የተነሱት የትግራይና የአማራ ክልልን ወሰን ውዝግብ በቶሎ ባለመቅጨት ትግሬዎችን ለጥቃት አጋልጠሃል በሚል እንደሆነም ተመልክቷል።
ከወሰን ውዝግቡ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በጎንደርና በባህርዳር ስለተገደሉት ዜጎች ግን የተነሳ ጉዳይ አለመኖሩ ታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ብቻ ወደ አንድ ሺ ሰዎች ባለቁበት ድርጊት ውስጥ የግድያው መሪ ተዋናይ ስለሆኑት የህወሃት ሰዎች የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የጠየቀው ወይንም የገሰጸው አካል ስለመኖሩ አልተዘገበም።
ከአማራና ከትግራይ ወሰን ውዝግብ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በጎንደርና በባህርዳር ስለተገደሉት ዜጎችም ማዕከላዊ ኮሚቴው ያለው አንዳችም ነገር የለም።
የክልሎቹን የወሰን ውዝግብ በቶሎ ባለመቅጨት ትግሬዎችን ለጥቃት አጋልጠሃል በሚል አቶ አባይ ወልዱን ከፓርቲው ሊቀመንበርነትና ስራ አስፈጻሚነት ከማንሳት ውጪ።
በመቀሌ የመከረው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ሂስና ግለሂስ በውስጡ ስለተንሰራፋው ሌብነት ምንም ሳያነሳ የርምጃ ትኩረቱን ያደረገው በክልሉ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ አመራሮችን ከስልጣን ማሰናበት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይልቁንም በሃገሪቱ ከሚካሄደው ፍጅትና ግድያ ጋር በተያያዘ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የሀገሪቱ ደህንነት መስሪያ ቤት ዋና ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ በፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት እንዲቀጥሉ ተወስኗል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን አቶ አባይ ወልዱ ላይ የሚደረገውን ግምገማ ተቃውመው ስብሰባውን ረግጠው በመውጣታቸው ከማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም ከስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው ታግደዋል።
የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የሕወሃት ጉባኤ በመሆኑ መባረር አለመባረራቸው የሚወሰነውም በዚሁ ወቅት እንደሆነ ታውቋል።
አቶ አባይ ወልዱን በተመለከተ አዲስ የክልል ፕሬዝዳንት ለትግራይ እንደሚሾምም ለማወቅ ተችሏል።