(ኢሳት ዜና–ሕዳር 18/2010)በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አታሼ ተስፋኪሮስ ሃይሉ ገብረማርያም በኢትዮጵያና በቱርክ መሃል ጦርነት እጭራለሁ ሲሉ ማስፈራራታቸው ተገለጸ።
አታሼው ይህን ያሉት በስካር መኪና ሲያሽከረክሩ አደጋ ማድረሳቸውን ተከትሎ በፖሊስ በመጠየቃቸው ነው።
በቱርክ አንካራ ቅዳሜ ለሌት አደጋውን ያደርሱት አቶ ተስፋኪሮስ ሁለት ተሽከርካሪዎችን የገጩ ሲሆን አንድ ሰው ማቁሰላቸውም ታውቋል።
በሎሳንጀለስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ሰርተዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ቆይተዋል። አሁን በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አታሼ በሚል ሃላፊነት እየሰሩ ናቸው። አቶ ተስፋኪሮስ ሃይሉ ገብረማርያም።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በበርካታ ሀገራት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ የአምባሳደሮቹን እንቅስቃሴ በቅርበት እንዲከታተሉ ከሚደረጉ የህወሀት ደህንነቶች አንዱ አቶ ተስፋኪሮስ ናቸው።
በተለይም የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ አምባሳደሮች በሚመደቡባቸው ሀገራት ከአምባሳደሩ በላይ የሚያዙትና የሚወስኑት እነዚህ በአታሼ ስም የተመደቡ የህወሀት የደህንነት ሰዎች መሆናቸውን ከውስጥ ምንጭ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ተስፋኪሮስ ሃይሉ ገብረማርያም በቱርክ የሚገኙትን አምባሳደር አያሌው ጎበዜን እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ የተመደቡ ሲሆን በይፋ የተመዘገበው የሃላፊነት ቦታቸው የኤምባሲው አታሼ የሚል እንደሆነም ታውቋል።
አቶ ተስፋኪሮስ ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በቱርክ መዲና አንካራ ከመጠን ያለፈ አልኮል ጠጥተው የሰሌዳ ቁጥር 06ዲሲ6124 ተሽከርካሪ ቱኒዚያን ጎዳና ላይ ሲነዱ መኪና ይገጫሉ። በዚህም አላበቁም።
አምልጠው በፍጥነት ሲጓዙ ሁለተኛ መኪና ይመታሉ። ሁለተኛው የተመታው ታክሲ ነበር። ሹፌሩ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ይወሰዳል።
የአይን እማኞችን ጠቅሰው የዘገቡ የአንካራ የመገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት በአካባቢው የፖሊስ ሃይል የደረሰው ወዲያውኑ ነበር።
ከዚያም አቶ ተስፋኪሮስን ከመኪና እንዲወርዱ ይደረጋሉ። ፖሊስ የአልኮል መጠን ምርመራ እንዲያደርጉም ይጠይቃቸዋል። አቶ ተስፋኪሮስ ግን አሻፈረኝ አሉ።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለስልጣን ስለሆንኩ ምርመራውን እንዳደርግ አልገደድም ሲሉም ገለጹ።
በሁኔታው ግራ የተጋቡት የቱርክ ፖሊሶች አደጋ ማድረሳቸውንና ሰው መጎዳቱን በማስረዳት ላይ እያሉ አቶ ተስፋኪሮስ በስካር ውስጥ እንዳሉ ማስፈራራት መጀመራቸውን ነው የአይን እማኞች የሚገልጹት።
በቱርክና በኢትዮጵያ መሃል የዲፕሎማሲ ቀውስ እንዲፈጠር አደርጋለሁ በማለት ያስፈራሩት አቶ ተስፋኪሮስ በሁለቱ ሀገራት መሃል ጦርነት እቀሰቅሳለሁ ሲሉም ማስጠንቀቃቸው ተጠቅሷል።
ጉዳዩ በፖሊስ የተያዘ ቢሆንም አቶ ተስፋኪሮስ በፈጸሙት ወንጀል የሚገጥማቸውን ውሳኔ በተመለከተ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።
በዲፕሎማት ያለመታሰር መብት ቢኖራቸውም ከሀገር ሊባረሩ እንደሚችሉ ግን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አቶ ተስፋኪሮስ በአልኮል ተገፋፍተው በፈጸሙት ወንጀል ሲጠየቁ ጦርነት እጭራለሁ ማለታቸው ግን አነጋጋሪ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አታሼ የነበሩት የህውሀቱ አቶ ሰለሞን ታደሰ ኤምባሲው ውስጥ በተገኙ ሰልፈኞች ላይ ጥይት በመተኮሳቸው በ48ሰዓት ውስጥ ከአሜሪካ መባረራቸው የሚታወስ ነው።