(ኢሳት ዜና–ሕዳር 4/2010) በአለም ላይ እጅግ በጣም ጨካኝ የሚባል የፖሊስ ሃይል ከሚገኝባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን አንድ አለም አቀፍ ጥናት አመለከተ።
በጥናቱ ናይጄሪያ በአለም የመጨረሻዋ ሆና ተመዝግባለች።
የፖሊስ ሳይንስ ማህበር ከኢኮኖሚና ሰላም ተቋም ጋር በጋራ ይፋ ባደረጉት የጸጥታና ፖሊስ ደረጃ ኢትዮጵያ ከ127 ሀገራት ከስር 115ኛ ሆና ተመዝግባለች።
የፖሊስ ብቃትን፣ አሰራሩን እንዲሁም ሕጋዊነቱንና ውጤቱን በመገምገምና በመተንተን ጥናቱን ይፋ የሚያደርገው የፖሊስ ሳይንስ ማህበር የአውሮፓውያኑ 2016 ሪፖርቱንም ይፋ አድርጓል።
የአለም ጸጥታና ፖሊስ ደረጃ 127 ሀገራት የተካተቱ ሲሆን በጥናቱ መሰረት በአለም እጅግ መጥፎ የሚባል የፖሊስ ሃይል ያለባት ሀገር ናይጄሪያ ሆና ተመዝግባለች።
የፖሊስ ሳይንስ ማህበርና የኢኮኖሚ ጸጥታ ተቋም በጋራ ይፋ ባደረጉት አመታዊ ሪፖርት ከአፍሪካ ሀገራት በፖሊሲያዊ ተግባርና ውጤት ከፍተኛ ተብለው በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሱት ሀገራት ቦትስዋና፣ሩዋንዳ፣አልጄሪያ፣ሴኔጋል፣ቱኒዚያ፣ግብጽ፣ቦርኪናፋሶ፣ጋና፣ደቡብአፍሪካና ማሊ ናቸው።
ኢትዮጵያ ደግሞ ከመጨረሻዎቹ 10 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ተመድባለች።
በፖሊሲያዊ ብቃት፣አሰራር እንዲሁም ሕጋዊነትና ውጤት ላይ በተደረገው ጥናት መጥፎ በሚል ከአለም በመጨረሻ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃስ ሆናለች።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአፍሪካም ከአለምም ከመጨረሻ ሁለተኛ ሆናለች።
በ127ቱ ሀገራት በተደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ከስር 115ኛ ስትሆን ኬንያ እንዲሁም ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ በታች በ124ኛና በ125ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።