(ኢሳት ዜና–ህዳር 1/2010)በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተካተቱበት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሀገሪቱ ያሉትን ችግሮች ይፈታል የተባለ አዲስ እቅድ አወጣ።
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ያወጣውን አዲስ እቅድ በተመለከተ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የጸጥታ ሃይሎች ከእንግዲህ የሚካሄዱ ህገ ወጥ ሰልፎችን ለማስቆም እንዲችሉ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።
እስካሁን ለጠፋ ህይወትና ንብረት የሚጠየቁና ለሕግ የሚቀርቡ አካላት እንደሚኖሩም አቶ ሲራጅ ገልጸዋል።
ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚያካሂዱት አመጽ እንዲቆም ይደረጋልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ሕዝባዊ አመጽ አንዴ በሀይል ሌላ ጊዜ ደግሞ ያልተፈጠረ በማስመሰል ለመከላከል ሲማስን የነበረውና በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ ብዙ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
በአስቸኳይ አዋጁ ጭምር የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን ያልቻለው አገዛዝ ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ውሏል፣የሀገሪቱ ሰላምም አስተማማኝ ነው ሲልም ነበር።
አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የሕዝብ ቁጣ ለማፈን አዲስ እቅድ ነድፌያለሁ እያለ ነው።
አዲስ እቅድ ደግሞ ተነደፈ የተባለው በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሚባለው በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የሚመራ ሆኖ በውስጡ የሀገር መከላከያ ሚኒስትርን፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን፣የመረጃ ደህንነት መስሪያ ቤትን፣የኢህአዴግ ጽህፈት ቤትንና ሌሎች የጸጥታ አላካትን ያካተተ ነው።
በአሁኑ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የክልሎች የጸጥታ አካላትም ተሳትፈውበታል።
እናም የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለውን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት በሚል የተለያዩ ርምጃዎችን እንደሚወስድ ገልጿል።
የምክር ቤቱን ውሳኔ አስመልክተው የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ እንዳሉት ከአሁን በኋላ የሚካሄዱ ሰልፎች የሚያስከትሉትን ችግር ለመከላከል የጸጥታ አካላት ተቀናጅተው ርምጃ ይወስዳሉ።
እስካሁን የሚካሄዱ ሰልፎችም ሕገወጦች ናቸው ብለዋል።
በኦሮሚያና ሶማሌ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ለጠፋው ሕይወትና ንብረትም ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት እንደሚኖሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ገልጸዋል።
ከኦሮሚያና ሶማሌ የተፈናቀሉት ከ7 መቶ ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ወደነበሩበት ይመለሳሉ ብለዋል።
በኬላዎች፣በአውራጎዳናዎች እንዲሁም ከክልል ክልል በሚደረጉ ዝውውሮች ሰላም ጠፍቷል ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ባወጣው አዲስ እቅድ በዘላቂነት ይፈታል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሲራጅ በአዲሱ እቅድ የሚታሰር ሰው እንዳለ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የጸጥታ ሃይሎች ይወስዳሉ ስላሉ ርምጃ ግን ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።