ፍልሰተኞችን ለመርዳት የሚመደበው በጀት በሕወሃት ደህንነት መስሪያ ቤት እየተመዘበረ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010)በኢትዮጵያ ያሉና አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ፍልሰተኞችን ለመርዳት የተባበሩት መንግስታት የሚመድበው በጀት በሕወሃት ደህንነት መስሪያ ቤት እየተመዘበረ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

ይህው በጀት ግን በደህንነት መስሪያ ቤቱ እየተመዘበረ በየአመቱ ያልተወራረደ በሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር እየባከነ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን በርካታ ተሽከርካሪዎች በደህንነት መስሪያ ቤቱ ለግድያና ለአፈና እንዲሁም ለእስር ከመዋላቸው ሌላ ለባለስልጣናት የግል መገልገያነት እንደሚውሉም ለማወቅ ተችሏል።

በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ መስሪያ ቤት ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመቀናጀት 850 ሺ ፍልሰተኞችን ያስተዳደራል።

በ26 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙት ከደቡብ ሱዳን፣ከሶማሊያና ኤርትራ ለተሰደዱ ፍልሰተኞች በጀት የሚመደብለትም በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን/ዩ ኤን ኤች ሲ አር/አማካኝነት ነው።

በዚሁም የምግብ፣የጤናና የአካባቢ ጥበቃ አገልግሎቶችን መስጠት የደህንነት መስሪያ ቤቱ መጠላያዎቹን እንዲያስተዳደር ተደርጓል።

በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚዘንብለት ይህ የደህንነት ቤት ግን በጀቱን እየመዘበረና ከታለመለት አላማ ውጭ እየተጠቀመበት መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

እንደ ምንጮቹ ገለጻ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ድርጅት በደህንነት መስሪያ ቤቱ ስር ሆኖ የተባበሩት መንግስታት በጀትን ስለሚያባክን በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች ሳይወራረዱ በእንጥልጥል ላይ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ይህንኑ በተመለከተ ለደህንነት መስሪያ ቤቱ ማመልከቱም ነው የሚነገረው።

ይህ ብቻ አይደለም የተባበሩት መንግስታት ለስራ ማስኬጂያ በሚል ለስደተኞች መርጃ ለደህንነት መስሪያ ቤቱ የሰጣቸው በርካታ ተሽከርካሪዎችም ለግድያ፣ለአፈናና ለእስር ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተጠቁሟል።

በደህንነት መስሪያ ቤቱ ሹሞች የአቶ ጌታቸው አሰፋ የቀድሞ ባልደረባ አቶ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስና የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘይኑ ጀማል ቤተሰቦችና ልጆች በሊሴ ገብረማርያምና በውጭ ሀገር ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈለ እንደሚማሩም ታውቋል።

አቶ ዘይኑ ጀማል በፊዚክስ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ የደህንነት መስሪያ ቤቱን ተቀላቅለው በኬንያ የደህንነት አታሼ በመሆን በርካታ ስደተኞችን ያስገደሉና ያሳፈኑ መሆናቸውም ነው የሚነገረው።

በደህንነት መስሪያ ቤቱ የሚመራው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች መስሪያ ቤት ከተባበሩት መንግስታት የሚያገኘውን ገንዘብ የሚመዘብረው ለኮንስትራክሽን ከሚውሉ ግብአቶችና ከልዩ ወጭዎች የሚመደበውን ነው።

ይህው መስሪያ ቤት የሕወሃት አባላትን ከኤርትራ የተሰደዱ ናቸው በሚል በርካታ የትግራይ ተወላጆችን በዩ ኤን ኤች ሲ አር አማካኝነት ወደ ውጭ እንደሚልክም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።