(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 27/2010)በሰሜን ጎንደር ዞን በጭልጋ በህወሀት መንግስት አማካኝነት ለማካለል በታቀደው የቅማንት አስተዳደር ጉዳይ ላይ የተጠራውን ስብሰባ ነዋሪው ረግጦ መውጣቱ ተገለጸ።
ያለህዝበ ውሳኔና ፍቃድ በህወሀት መንግስት የተካለሉትን 42 ቀበሌዎች የሚያቅፈው የቅማንት ልዩ ዞን በሚል ለሚዋቀረው አዲሱ አስተዳደር በዋና ከተማነት በተመረጠችው አይከል ከተማ በህዝብና በመንግስት ባለስልጣናት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ መፈጠሩን ለማወቅ ተችሏል።
የቅማንት ማህበረሰብ በብዛት ይገኝበታል በተባለው የአይከል ከተማ ይህ ተቃውሞ መነሳቱ የህወሀትን መንግስት እቅድ ሊያከሽፈው ይችላል ተብሏል።
ሰሞኑን የቅማንትን አዲስ አስተዳደር ተፈጻሚ ለማድረግ በህወሃት መንግስት የሚደገፈው የቅማንት ኮሚቴና የደህንነት ሰዎች አይከል ከተማ ገብተዋል።
የፌደራል መንግስትና የአማራ ክልል ባለስልጣናትም ለዚሁ ጉዳይ አይከል መግባታቸው ታውቋል።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ አዲሱን የቅማንት አስተዳደር በተመለከተ በጋራ ስለሚሰሩ ጉዳዮች ለመምከር የአይከል ከተማ ህዝብ ስብሰባ ተጠርቶ እንደነበረ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ህዝቡ ሳያውቀው፣ፍላጎቱና ውሳኔው ሳይጠየቅ አይከል ከተማ በህወሀት መንግስት የተዋቀረው የቅማንት አዲስ አስተዳደር ዋና ከተማ እንድትሆን መወሰኑ ተቃውሞ ቀስቅሷል።
በአይከል ከተማ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም የህወሀት መንግስትን ዕቅድ ፈጽሞ እንዳልተቀበሉት ይነገራል።
በአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በአንድነት የታቀደውን አዲስ አስተዳደር እንደማይቀበሉት በተጠራው ስብሰባ ላይ አቋማቸውን አሳውቀዋል።
ይሁንና ከፌደራልና ከክልል የመጡት የህወሀት መንግስት ባለስልጣናት የህዝቡን ተቃውሞ ወደ ጎን በማድረግ በመንግስት በኩል የተወሰነው ተፈጻሚ እንደሚሆን ሲገልጹ ህዝቡ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተለይም በከተማዋ ብዙ ቁጥር ያለው የሙስሊም ነዋሪ፡ ‘’እኛ አንድ ነን። ለምን ትከፋፍሉናላችሁ?’’ በሚል ተቃውሞ ማሰማት በመጀመራቸው ስብሰባው መደፍረሱንና እነሱን ተከትለው ሌሎች ተሰብሳቢዎችም ድምጻቸውን በማሰማት የህወሀትን መንግስት ዕቅድ ማውገዛቸውን ነው በስብሰባው ላይ የነበሩት የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
ይህን ተከትሎም በአዳራሹ የነበረው አብዛኛው ታዳሚ መድረኩን ረግጦ የወጣ ሲሆን ስብሰባው መቀጠል ሳይችል መቋረጡንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከቅዳሜ ጀምሮ ካድሬዎች በታጣቂዎች ታጅበው ቤት ለቤት በመዞር ህዝቡን ሲያስፈራሩት እንደነበርም ታውቋል።
ህዝቡ ቀድሞውኑ አዲሱን የቅማንት አስተዳደር ባልተቀበለበት ሁኔታ አይከልን ዋና ከተማ ለማድረግ የሚካሄደው ወከባ በአካባቢው ውጥረት ማንገሱም ተገልጿል።
ዘግይቶ የደረሰን ዜና እንደሚያመለክተው ዛሬም የህወሀት ደህንነቶች ህዝቡን እያስፈራሩና አይከል የቅማንት ልዩ ዞን ዋና ከተማ እንድትሆን ተስማምቼያለሁ የሚል ወረቀት በግዳጅ ለማስፈረም ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታውቋል።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው ህዝቡ አሻፈረኝ የሚል ከሆነ የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስ መታቀዱንና ነዋሪው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡም ተመልክቷል።
ህወሀት ያለህዝብ ፈቃድ የቅማንት አስተዳደርን በማካለል ተፈጻሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ይህም በታላቋ ትግራይ ውስጥ የሚካተቱ መሬቶችን ለመውሰድ ታሳቢ ተደርጎ የተዘረጋ እቅድ እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ።