ኡስታዝ አብዱልመጂድ ሁሴን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 27/2010) ታዋቂው የእስልምና እምነት መምህር ኡስታዝ አብዱልመጂድ ሁሴን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በቴሌቪዥን በሚያቀርቡት የእልምና ትምህርቶች የሚታወቁት እኚህ መምህርና ሰባኪ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ትላንት ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ኮልፌ የሙስሊሞች መካነ መቃብር በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈጽሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አንጋፋው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

የቀብር ስነስርአቱም በአዲስ አበባ ቀጨኔ ደብረሰላም መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን ቅዳሜ ዕለት ተፈጽሟል።

የእምነቱ ሰዎች ታላቅ መምህር ይሏቸዋል። ድንቅ ሰባኪም። በኢትዮጵያ ሙስሊሞች እጅግ ተወዳጅ የሃይማኖቱ አስተማሪ እንደሆኑ ይነገራል።

ከወጣት የእምነቱ መምህራን ላቅ ያለ ደረጃ ላይ የደረሱ፣ በማስተማር ብቃታቸውና ስለእምነቱ ባላቸው የጠለቀ ዕውቀት ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር የተለገሳቸው መምህር ነበሩ – ኡስታዝ አብዱልመጅድ ሁሴን።

በሱዳን ዩኒቨርስቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በአወሊያ የእስልምና ትምህርት ቤትም እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

ኡስታዝ አብዱል መጂድ በተለይ በስፋት የሚታወቁት በአፍሪካ ቲቪ ላይ በሚያቀርቧቸው ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ነው።

ከሴቶች መብት አንጻር የአደባባይ ተሟጋች እንደነበሩ ይነገራል። በዚሁ የአፍሪካ ቲቪ ላይ ሴቶችን በማንቃት ማህበረሰባዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል በሚል አጀንዳ ተከታታይ የማስተማሪያ መድረኮችን በመክፈት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተከታዮችን ቀልብ መግዛት እንደቻሉም በህይወት ታሪካቸው ላይ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከወጣቱ ትውልድ ጋር የሚያደርጉት የለውጥ እንቅስቃሴም በአርአያነት የሚነሳላቸው ታላቅ ተግባር እንደሆነ ያነጋገርናቸው የእምነቱ አዋቂዎች ገልጸዋል።

በተለይም ወጣቶችን ለመልካም ነገር እንዲተጉ፣ ከአልባሌ ነገሮች ራሳቸውን እንዲያቅቡ በማድረግ ላይ ባተኮረው ትምህርታዊ እንቅስቃሴያቸው የብዙዎች ወጣቶች ህይወት መቀየሩንም ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ይናገራሉ።

በዲቪዲና በሲዲ በሚሰራጩ የድምጽና የምስል ተከታታይ ትምህርቶችም ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ስማቸው ይነሳል–ኡስታዝ አብዱልመጂድ ሁሴን።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል እንቅስቃሴ ሲጀመር ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄዱት ኡስታዝ አብዱልመጂድ በህመም አልጋ እስከያዙበት ቅርብ ጊዜ ድረስ እዚያው በሳዑዲ አረቢያ ቆይተዋል።

ወደሀገር ቤት ከመጡ በኋላም ህክምና ላይ ቢቆዩም ጤንነታቸው ሊሻሻል ባለመቻሉ ወደቱርክ የተወሰዱ ሲሆን በዚያም ህክምናውን ሲከታተሉ ቆይተው ትላንት ማረፋቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊሞች መካነ መቃብር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች፣ወዳጆቻቸውና ጓደኞቻቸው በተገኙበት የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈጽሟል።

ኡስታዝ አብዱልመጂድ ሁሴን ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አንጋፋው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል። በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ውስጥ ከ1985 ጀምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች በአዘጋጅነትና በጸሀፊነት ሲሳተፍ የነበረው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ ከዚህ አለም በሞት የተለየው ባደረበት ህመም ምክንያት እንደሆነ ታውቋል።

አርብ ጥቅምት 24/2010 ከዚህ አለም በሞት የተለየው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ በጦማር፣በኢትዮጵና በልዩ ልዩ የነጻ ፕሬዝ ጋዜጦች ላይ በአዘጋጅነትና በጸሃፊነት ተሳትፏል።

በነጻ ፕሬስ ውስጥ ጉልህ ሚና ከነበራቸውና ቀደምት ከነበሩት ጋዜጠኞች አንዱ የነበረው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ ከአምስት ወራት በፊት በገጠመው የጤና እክል አንድ እግሩን ማጣቱም ታወቃል።

እግሩ መቆረጡን ተከትሎ በውጭ የሚገኙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ባደረጉለት ድጋፍ ሰው ሰራሽ እግር ለማስገጠም በዝግጅት ላይ ሳለ ህይወቱ ማለፉም ተመልክቷል።

በነሀሴ ወር 2009 እግሩን በተቆረጠበት ወቅት በውጭ ሀገር የሚገኙ የነጻ ፕሬስ ባልደረቦች አስተባባሪነት የተደረገለትን ድጋፍ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ መድረኮች ምስጋና ያቀረበው ግርማዬነህ ማሞ ይህን መልዕክት ባስተላለፈ ሳምንት ባልሞላ ግዜ ውስጥ በመተንፈሻ አካሉ ላይ በገጠመው ችግር ህይወቱ ማለፉ ታውቋል።

ከሞት አፋፍ መልሳችሁ በሕይወት ለመኖር የሚያስችለኝን እርዳታ ስላደረጋችሁልኝ በሕያው እግዚአብሄር ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብሎ ነበር አንጋፋው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ።

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ የቀብር ስነስርአት ቅዳሜ ጥቅምት 25/2010 በቀጨኔ ደብረሰላም መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።