(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 14/2010) የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታና ምክትል ሊቀመንበሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ ወደ ሱዳን ካርቱም ያመሩት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር ሳይሆን የአፍሪካ ሕብረት ባቀረበላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑን አረጋገጡ።
አመራሮቹ በተለይ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ህብረቱ ግብዣውን ያደረገላቸው በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያደረጉትን ጥናት መነሻ በማድረግ በሱዳን ካርቱም ለኤክስፐርቶች በተዘጋጀው መድረክ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሚስጥር በሱዳን ካርቱም ድርድር ማድረጋቸው የተገለጸው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ኦዴግ አመራሮች አቶ ሌንጮ ለታና ዶክተር ዲማ ነገዎ በጉዳዩ ላይ ለኢሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታና ምክትል ሊቀመንበሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ ካርቱም መሔዳቸውን ለኢሳት ያረጋገጡ ሲሆን ጉዟቸው ግን ለድርድር ሳይሆን የአፍሪካ ሕብረት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ በተደረገላቸው ግብዣ መሆኑን ተናግረዋል።
ስብሰባው ለኤክስፐርቶች የተዘጋጀ በመሆኑ ሁለቱም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያደረጉትን ጥናት መነሻ በማድረግ መጋበዛቸውንም አስረድተዋል።
በስብሰባው ስፍራ አንድም የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን ወይንም ልውጥ እንዳልነበር የገለጹት አቶ ሌንጮ ለታና ዶክተር ዲማ ነገዎ ግብዣው በግል በባለሙያነት የመጣላቸው ቢሆንም የተጓዙት ግን ፓርቲያቸውን አሳውቀው መሆኑን ጠቁመዋል።
ስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት መደራደር ከፈለገ በቅድሚያ ያሰራቸውን ፈቶ ከነሱ ጋር ይደራደር ሲሉም አቶ ሌንጮ ለታ ተናግረዋል።
ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ችግር ሰፊና ውስብስብ በመሆኑና ከአንድ ወገን ጋር በመደራደር ስለማይፈታ በተናጠል ግብዣም ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደለንም ብለዋል።