በኬንያ ምርጫው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ተጠየቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 14/2010) በኬንያ ሀሙስ በድጋሚ ሊደረግ የታሰበውን ምርጫ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫውን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲያሸጋግር ተጠየቀ።

ፍርድ ቤቱ በሶስት ኬንያውያን የቀረበውን ይህን ሀሳብ ነገ ያያል ተብሎም ይጠበቃል።

በስልጣን ላይ ያሉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደግሞ ምርጫው በተወሰነለት ጊዜ እንዲካሄድ በመወትወት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በኬንያ ሀሙስ ሊደረግ የታሰበው ምርጫ ተአማኒነት ላይኖረው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ባለበት በዚህ ወቅት የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫውን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ በመጠየቅ ላይ ነው።

ፍርድ ቤቱ በሶስት ኬንያውያን የቀረበውንና ምርጫው እንዲተላለፍ የሚጠይቅን ጉዳይ ነገ እንደሚያይ ሲጠበቅ ባለፈው ምርጫ አሸናፊ ሆነው ነገር ግን ማጭበርበር ተፈጽሞበታል ተብሎ የተሻረባቸው ተቀማጩ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫው እንዲካሄድ እየወተወቱ ይገኛል።

የተቃዋሚው እጩ ራይላ ኦዲንጋ ግን በምርጫው እንደማይሳተፉ ደጋግመው አስታውቀዋል።

ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጥያቄ ካቀረቡት ሶስት ግለሰቦች ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ከሊፍ ካሊፋ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ነሀሴ የተካሄደውን የምርጫ ውጤት ሲሽር በግልጽ እንዳስቀመጠው የድጋሚው ምርጫ የሚካሄደው ተአማኒነት ያለውና መጣራት የሚችል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው በማለቱ ነው።

አሁን ግን ሁኔታዎች ያንን እንደማያመለክቱና ምርጫው የተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የገባ በመሆኑ ወደ ሌላ ጊዜ ሊያስተላልፍ ይገባዋል ብለዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አክለውም የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫውን ተአማኒነት ባለው መልኩ ለማካሄድ ማስተማመኛ መስጠት አልችልም ማለቱን አስታውሰዋል።

መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ በወሰደው ርምጃ ወደ 67 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውንና ሀገሪቱ ወደ ማህበራዊ መፈረካከስ እያመራች መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህ ሁኔታ ሐሙስ ምርጫውን ማካሄድ ደግሞ ሀገሪቱን ለበለጠ ሁከትና ብጥብጥ ይዳርጋታል ሲሉ ካሊፍ አስጠንቅቀዋል።

የምርጫ ኮሚሽኑ አስተማማኝ ምርጫ ማካሄድ መቻሉን እርግጠኛ መሆን እስከሚቻል ድርስ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ በኬንያ ዋና ከተማ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስና የማስጠንቀቂያ ተኩስ በመተኮስ ለመበተን መሞከሩ ታውቋል።

በነሀሴ ሁለት ከተደረገውና ከተሻረው ምርጫ ወዲህ በተነሳው ብጥብጥ እስካሁን 67 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።