(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 14/2010) በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንና ኢህአዴግም እያለቀለት መሆኑን የቀድሞው የሕወሃት አመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት ገለጹ።
ኢህአዴግ እየገዛ ያለው በደህንነቱና በሰራዊቱ አማካኝነት እንደሆነም ተናግረዋል።
ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ ገብሩ አስራት ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች የሚለው ሟርት ግን ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
እስከ 1993 የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ሀገር ውስጥ ከሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር።
በቃለ ምልልሱም በኢህአዴግ ውስጥ ሽኩቻው መበርታቱን፣እያንዳንዱም ስለራሱና ስለአካባቢው ብቻ እየተጨነቀ ስልጣኑንና ሀብቱን ላለማስነካት እየተፍጨረጨረ መሆኑን በዝርዝር አስቀምጠዋል።
የሕዝቡ አልገዛ ባይነትም ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተዋል።
አቶ ገብሩ የእርስ በርስ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አልሸሸጉም።
ኢህአዴግ እንዳበቃለት የሚያጠራጥር አለመሆኑን የተናገሩት የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩትና የአሁኑ የአረና አመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት አሁን በኢትዮጵያ ያለው ችግር ኢህአዴግን ማን ይተካዋል የሚለው ምላሽ አለማግኘቱ እንደሆነም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የጎደለ ነገር ቢኖር ኢሕአዴግን የተመለከተ ጉዳይ ነው።ይህ ጉዳይ ለሁሉም አሳሳቢ ሆኗል በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ገብሩ አስራት ይህ ማለት በሀገሪቱ ህልውና ላይ አደጋ ይደቅናል ማለት እንዳልሆነም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚለውንም ሟርት አልቀበለውም ያሉት አቶ ገብሩ ኢትዮጵያ ከኢህአዴግ በፊትም ኖራለች ሕዝቡም አብሮ መኖር ይፈልጋል ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።
ፖለቲከኞች ግን ይህንን የሚያላላ ድርጊት እየፈጸሙ ነው በማለት ወቅሰዋል።
ኢህአዴግ ሲወድቅ የሲቪል አስተዳደሩ ስልጣኑን ሲያጣ ሰራዊት ሊመጣና ስልጣኑን ሊቆጣጠር እንደሚችል ገልጸዋል።