በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ካርታ በሚመለከተው አካል ያልጸደቀ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 13/2010) በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ካርታ በሚመለከተው አካል ያልጸደቀ መሆኑን መንግስት አስታወቀ።

ካርታው ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ብቻ ስራ ላይ ሊውል እንደሚችልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ለሶስተኛ ጊዜ የተሳሳተ የኢትዮጵያ ካርታ መጠቀሙን በማመን ይቅርታ በጠየቀበት ዘገባ በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ካርታ በሚመለከተው አካል ያልጸደቀ እንደሆነ የኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን መሐመድ አስታውቀዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን መሀመድ እንደገለጹት አሁን ያለው ካርታ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች መጠቀም የሚቻል ቢሆንም ሁሉም ክልሎች ተስማምተውበት የጸደቀ ካርታ አይደለም ብለዋል።

ለወደፊት ሁሉም ክልሎች የሚስማሙበት፣ ተገቢው የመንግስት አካላት ስምምነት የደረሱበትና ግልጽ የሆነ ወሰን የሚያሳይ ካርታ ተዘጋጅቶ እንደሚጸድቅ አስታውቀዋል።

በመጪው የካቲት የሚካሄደውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በመጠቀም የክልሎችን ወሰን የሚያሳይ ካርታ ማዛጋጀትም ቀጣይ ስራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሶስተኛ ጊዜ የተሳሳተ ካርታ ተጠቅሟል በተባለው ጋዜጠኛ ላይ ርምጃ መወሰዱንም የኢሳት ምንጮች ጠቁመዋል።

ዝርክርክ ነው በሚባለው የኢቲቪ መረጃ አያያዝ ውስጥ ካርታውን ከፋይል ማስወገድ የተሳናቸው የበላይ ሃላፊዎች ምንም አይነት ርምጃ ሳይወሰድባቸው ጋዜጠኛውን መቅጣት በተቋሙ ሰራተኞች ውስጥ ቅሬታ መፍጠሩን ምንጮቻችን ጨምረው ገልጸዋል።

ሌሎች አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው የራሱን ድብቅ ተግባር ለማስፈጸም በማሰብ አስቀድሞ ይህን ካርታ የነደፈው የህወሃት አገዛዝ ዛሬ ላይ ጭራሹኑ የኢትዮጵያ ካርታ በሚመለከተው አካል ያልጸደቀ ነው ማለቱ አጠያያቂ ነው ሲሉ ገልጸውታል።