(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 10/2010) በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ለአገዛዙ ቁልፍ በሆኑ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ልዩ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ልዩ ጥበቃው ከአገዛዙ ባፈነገጡ ባለስልጣናት መፈንቅለ መንግስት ሊካሄድ ይችላል በሚል ስጋት ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ጭንቀትና ውጥረትን ፈጥሯል።
የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት የሕዝቡ ተቃውሞ የፈጠረው ቀውስ በአገዛዙ ባለስልጣናት በኩልም የእርስ በርስ ሽኩቻና አለመተማመኑ አይሏል።
እናም ድንገት ባልታሰበ ሁኔታ የመፈንቅለ መንግስት ሊከሰት ይችላል በሚል በደህንነት ሃይሎች የታገዘ ልዩ ጥበቃ ቁልፍ በሆኑ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።
ልዩ ጥበቃ በስውርና በግልጽ እየተካሄደባቸው ያሉ መስሪያ ቤቶች የመንግስት መገናኛ ብዙሃንንም ይጨምራል።
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በአይነ ቁራኛ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በልዩ ጥበቃው በየጊዜው የሚቀያየሩ የይለፍ ቃላት ለጥበቃ ሰራተኞች ይሰጣሉ።
የደህንነት አባላትም በስውር ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የጸጥታ ሰራተኞችን እየቀያየሩ መሆናቸው ነው የተነገረው።
በተለይ ደግሞ ከሕወሃት ውጭ ያሉ ሌሎች ብሔሮች እምነት ስለማይጣልባቸው አንድ ቦታ ተወስነው እንዳይሰሩ ይደረጋል ተብሏል።
እንደ ቅርብ ምንጮች ገለጻ አሁን በሀገሪቱ እየታየ ያለው ልዩ ጥበቃ ምክንያቱ ድንገት መፈንቅለ መንግስት ሊካሄድ ይችላል በሚል ነው።
በኢትዮጵያ ባለው ውጥረት የአገዛዙ ባለስልጣናት እርስ በርስ እየተማመኑ አይደለም።በቡድንና በብሔር የተዋቀረውና በሕወሃት የበላይነት የሚመራው አገዛዝ የራሱን ባለስልጣናት መጠራጠሩ ስርአቱ እያበቃ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/አመራሮች መካከል ከፍተኛ የሀሳብ ልዩነት መኖሩን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አመራሮቹ በሀሳብ ተለያይተው ሲጨቃጨቁ ጉዳዩን ለማለዘብ ይህ የዲሞክራሲያችን መገለጫ ነው እያሉ አንዱ ከአንዱ ጋር ያለውን የአቋም ልዩነት ለማወቅ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ነው ተብሏል።