በኦሮሚያ ክልል እየተካሄዱ ያሉትን የተቃውሞ ሰልፎች ማን እንዳቀናበራቸው ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት10/2010)በኦሮሚያ ክልል እየተካሄዱ ያሉትን የተቃውሞ ሰልፎች ማን እንዳቀናበራቸውና አላማቸው ምን እንደሆነ ምርመራ ላይ መሆኑን የክልሉ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ በበኩሉ በኦሮሚያ ባለው ግጭት ሀገር አለን ማለት የማንችልበት ደረጃ ላይ እየደረስን በመሆኑ ያሳስበናል ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ተጠናክሮ የቀጠለውን ሕዝባዊ አመጽና የተቃውሞ ሰልፎች ተከትሎ የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የሕወሃት ንብረት ለሆነው ሬዲዮ ፋና መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አዲሱ በመግለጫቸውም የተካሄዱትን ሰልፎች ህገ ወጥ ከማለት ተቆጥበዋል።

በሰልፎቹ ላይ ሁከት እንዲፈጠር ያደረጉት አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰልፎቹን ማን አቀናበረ?የሰልፎቹ አላማስ ምንድን ነው?ሰልፈኞቹን ወደ ሁከተኛነት እንዲቀየሩ ያደረጉ አካላትን ማን አሰማራ? የተከለከሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሰንደቅ አላማ የለጠፈና ያከፋፈለ ማነው የሚለውን ፖሊስ ምርመራውን ካጠናቀቀ በኋላ ሊገለጽ እንደሚችል አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ መግለጫዎች ግን ፖሊስ ምርመራ ከማድረጉ በፊት ጸረ ሰላም ሀይሎችና አሸባሪዎች ፈጸሙት ሲባል መቆየቱ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት ለሕዝብ ጥያቄዎች ትኩረት በመስጠት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት ተመልሰው እንዲቋቋሙ ጠይቋል።

የኦፌኮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙላቱ ገመቹ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ግጭት በሕዝብ መካከል የተነሳ ሳይሆን መንግስት ሆን ብሎ የሕዝቡን ጥያቄዎች ላለመመለስ ያደረገው እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰሞኑን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ሀገር አለን ማለት የማንችልበት ደረጃ እያደረሰን በመሆኑ በእጅጉ ያሳስበናል ብለዋል።