በሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ይሰጣል የተባለው ብይን የኢትዮጵያና የስዊድን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ያበላሸዋል ተባለ

05 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ላይ  በሚቀጥለው ሳምንት  ረቡዕ ይሰጣል የተባለው ብይን ለወትሮው በቋፍ ላይ የሚገኘውን  የኢትዮጵያና የስዊድን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መውጫ ይበልጥ ያበላሸዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ገለጹ።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ለኢሳት ዘጋቢ እንዳሉት፤ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተፈጠረ ያለው መቃቃር በጋዜጠኞቹ ላይ በሚሰጠው ብይንም ሆነ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም።

በ ኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር የመጨረሻው ብይን መልካም ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በቅርቡ መናገራቸውን እንዴት ያዩታል? ተብለው የተጠየቁት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው፦” እርሳቸው ዲፕሎማት ከመሆናቸው አንፃር ከዚህ ውጪ የሆነ ነገር ይናገራሉ ተብሎ አይጠበቅም።አምባሳደሩ እስካሁን ድረስ ባለው የፍርድ ቤት ሂደት አንድም ነገር ለመናገር ፈቃደኛ ያልሆኑት፤ ነገን በተረጋጋና ውጤታማ  በሆነ መንገድ  እንዲያልቅ በዲፕሎማት ዓይናቸው ለማየት በመፈለጋቸው እንጂ፤ ቅሬታ ስለሌላቸው አይመስለኝም” ብለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው አክለውም፦“አምባሳደሩ የጠበቁት ተስፋ ይሆናል፤አይሆንም የሚለውን በሚቀጥለው ሳምንት የምናየው ቢሆንም፤ በኔ በኩል በጋዜጠኞቹ ላይ የተቆለለባቸውን የሀሰት ክስ  ፍርድ ቤቱ ከመቀበሉ አንፃር ብዙም ተስፋ አይታየኝም” ብለዋል።በሕገ-ወጥ መንገድ ያለቪዛ ወደ ኢትዮጵያ በመግባትና ለሽብርተኝነት ድጋፍ በመስጠት ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት የሁለቱ ሲዊዲናዊያን ጋዜጠኞች ማርቲን  ሽብየ እና ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን ካርል ፐርሰን ጠበቆች ሰሞኑን፤ አራት የመከላከያ ምስክሮች ፣ የድምፅና የምስል ማስረጃ እና የፅሑፍ ሰነዶችን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት ማቅረባቸው ይታወቃል።
ማክሰኞ ህዳር 26 እና ዕረቡ ህዳር 27 ቀን 2004ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ ተርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች   በሙያቸው  መረጃዎችን ሰብስበው የሚያቀርቡ ታዋቂ ፍሪላንስ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኞች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ “አፍሪካን ኦይል” የተባለው የስዊዲን የነዳጅ አውጪ ካምፓኒ ቀደም ሲል በሱዳን ውስጥ ሲንቀሳቀስ- ሰዎችን ያለፈቃዳቸው ከአካባቢያቸው በማፈናቀል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስሞታዎች ይቀርቡበት ስለነበር፤ በኦጋዴን ክልል በነዳጅ ፍለጋ ላይ ሲንቀሳቀስ እንዲህ ዓይነት ተግባር ማከናወን አለማከናወኑን በቦታው በመገኘት የአካባቢውን ሰዎች በማናገር የምርመራ ዘገባ ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን ካርል ፐርሰን፦” ማስተካከያ አለኝ”በማለት ባቀረበው አቤቱታ  ፦”ስለ እኔ ፖሊሶች የሰጡት ትርጉም የተዛባ ነው፤ ለምሳሌ እኔ ስለኢትዮጵያ መጽሐፍ እንደፃፍኩና በ2003ዓ.ም አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ እንደኖርኩ ገልፀዋል፤ ይህ ትክክል አይደለም፣ ስለኢትዮጵያ መፅሀፍ አልፃፍኩም፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ መጥቼ
አላውቅም፤ እንዲህ አይነት ቃል አልሰጠሁም፤ ከዚህም በላይ እኔ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር እንደተጋጨሁ ተጽፏል፤ ይህ ውሸት ነው፤ አልተጋጨሁም፤እንዲህ አይነት ቃል ለፖሊስ አልሰጠሁም፡፡ ይህንንም በአስተርጓሚ እንደተነገረኝና አምኜበት እንደፈረምኩ ተደርጓል ግን ውሸት ነው፡፡ ምንም ነገር ተተርጉሞ አልቀረበልኝም አልፈረምኩም ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የድምፅና የምስል ማስረጃዎችን ረቡዕ ህዳር 27 ቀን 2004ዓ.ም የተመለከተ ሲሆን የሰነድ ማስረጃዎችን ከተከላካይ ጠበቆች ተቀብሎ ዝርዝር ሀሳቡን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በማዘዝ፣ የክርክር ማቆሚያ ንግግር ለመስማትና መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 11 ቀን 2004ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡