የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ ከፓርቲ አመራርነት እራሳቸውን አገለሉ

  05 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ኢንጂነር ግዛቸው ይህን ያስታወቁት፤ ባለፈው እሁድ በዲ.አፍሪክ ሆቴል ብርሃን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ እና አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ  ፓርቲዎች በይፋ ውህደት በፈፀሙበት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው።

ኢንጂነር ግዛቸው በዕለቱ ለውህዱ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል ዕጩ ሆነው ቢቀርቡም፦ ‘‘እኔ የፖለቲካ ኃይሌ ከውስጤ ተሟጥጦ ስላለቀ፤ የብሄራዊ ምክር ቤት አባልም ሆነ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ መቀጠል አልችልም’’ ማለታቸው ተሰምቷል።

የኢንጂነር ግዛቸውን ውሳኔ ተከትሎ በጉባኤተኛው መካከል የተቃውሞ ጉምጉምታ ቢሰማም፤ እርሳቸው ግን  ለረጅም ጊዜ በፓርቲ አመራርነት መቆየታቸውን በመግለፅ፤ ኃላፊነታቸውን ማሸጋገር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

‘‘ኢንጂነር ግዛቸው በዚህ ሁኔታ ከፓርቲው ስራ መራቅ አይገባቸውም፣ ካላቸው የካበተ ልምድ አንፃር በፓርቲው ውስጥ በኃላፊነት መቀጠል ይገባቸዋል’’ የሚሉ አስተያየቶች ከጉባኤተኛው የተሰጡ ቢሆንም፤ በወቅቱ መድረኩን ይመራ ከነበረው አስመራጭ ኮሚቴ፦ ‘‘እርሳቸውን በግልም ሆነ በተለያየ መንገድ ማነጋገር ይቻላል። አሁን ግን አልፈልግም ማለታቸውን እንደመብት እንያዝላቸው’’ በማለት በኢንጂነር ግዛቸው ቦታ ሌላ ሰው መምረጥ እንደሚቻል ሀሳብ ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል በፓርቲው አዲስ ሕገ-ደንብ መሠረት በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሌሎች ሰዎችን እንደሁኔታው የማሳተፍ ስልጣን ስላላቸው፤ ኢንጂነር ግዛቸው በፓርቲው ውስጥ የመሳተፍ እድል እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

 በእለቱ ሁለቱ ፓርቲዎች በይፋ ውህደት ከፈፀሙ በኋላ የመድረክን ግንባር መሆን በይፋ በመደገፍ፤ አንድነትም በመድረኩ ውስጥ በግንባርነት እንዲቀጥል ተወስኗል።

ውህዱን ፓርቲ ለመምራት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲና ዶክተር ንጋት አስፋው በእጩነት ቀርበው የነበረ ሲሆን ፤ለጉባኤተኛው የምረጡኝ ዘመቻ እንዲያደርጉ ዕጩዎቹ በተጋበዙ ጊዜ ዶ/ር ንጋት ራሳቸውን ከዕጩነት አግልለዋል።

ዶ/ር ንጋት ‘‘በፖለቲካ ልምድም በእውቀትም አንጋፋ የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ እንዲመሩን ስለምፈልግ እኔን ልትመርጡ ያሰባችሁ ሁሉ ድምፃችሁን ለዶ/ር ነጋሶ ስጡልኝ’’ ብለዋል።

በቀጣይ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲና ዶ/ር ነጋሶ የምረጡኝ ቅስቀሳ ካካሄዱ በኋላ፤ ዶ/ር ነጋሶ 179 ለ29 በሆነ የድምፅ ልዩነት አሸናፊ በመሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ፓርቲውን በቅንነት ለማገልገል ቃለ-መሀላ ፈፅመዋል።

ምርጫው እንደተጠናቀቀ  አቶ ስዬ አብርሃና አቶ አክሎግ ግርግሬ  ለ አዲሱ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ለጉባኤተኞቹ በስካይፒ ፦” የእንኳን ደስ ያላችሁ!” መልእክት አስተላልፈዋል።
ከውህደቱ በኋላ የፕሬዝዳንት ምርጫውን ጨምሮ ሶስት አይነት ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትና የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ምርጫዎችም ተከናውነዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዱአለም አራጌና አቶ ናትናኤል አያሌውም የብሄራዊ ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ጉባኤው ተስማምቷል።
በዕለቱም ለብሔራዊ ምክር ቤት 40 ያህል ሰዎች፣ ለተለዋጭ ብሔራዊ ምክር ቤት 15 ሰዎች በድምሩ 55 ሰዎች ተመርጠዋል።
ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ እጅግ በርካታ ወጣቶች ኢንጂነር ግዛቸውን ከበው፦ ‘‘በዚህ ሁኔታ ጥለውን መሄድዎ አግባብ አይደለም’’ በማለት ኀሳባቸውን እንዲቀይሩ ሲያግባቡዋቸው ታይተዋል።