አቶ መለስ ዜናዊ የአፍሪካን የአካባቢ ጉባኤ ለመምራት የሞራል ብቃት የላቸውም ሲሉ አንድ ደቡብ አፍሪካዊት ጸሀፊ ገለጡ

  04 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ጃኒስ ዊንተር የተባሉት ጸሀፊ ደይሊ መቨሪክ በሚባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ባወጡት ጽሁፍ ፣ በደርባን የተካሄደው ኮፕ 17 የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ፣ ድንቅ የተባለ  ስምምነት አድርጓል።

የስምምነቱ ዋና ድል ተ ብሎ የተቆጠረው ደግሞ፣ የአካባቢ ጥበቃ ለማካሄድ የተፈቀደው ገንዘብ ነው።

መለስ ዜናዊ በጉባኤው ላይ ለአካባቢ ጥበቃ ተብሎ የተመደበው ገንዘብ አዲስ ገንዘብ አለመሆኑን ይልቁንም ከዚህ ቀደም ለእርዳታ ተብሎ ከተያዘው ላይ የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ ሀብታም አገሮች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመድቡ ተማጽኖ ነበር።

“ምንም እንኳ “ይላሉ ጸሀፊዋ ሲቀጥሉ” አፍሪካ በአየር ለውጥ ምክንያት ዋናዋ ተጎጂ አገር ብትሆንም፣  የተፈቀደው ገንዘብ ግን አምባገነኖችን በስልጣን ላይ ለማቆየት መዋል እንደሌለበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

መለስ ዜናዊ በአገሩ ውስጥ የሰብአዊ መብቶችን የረገጠ፣ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በጸረ ሽብርተኝነት ስም ለእስር የዳረገ፣ በምርጫ 97 ወቅት 199 ሰዎችን የገደለ፣ የእርዳታ እህልን ለፖለቲካ ድጋፍ መግዢያ ያዋለ፣ በቅርቡ ይፋ በሆነው የግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ሪፖርትም ባለፉት 7 አመታት ከኢትዮጵያ የተዘረፈ 11 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጭ መውጣቱ የተረገጋጠ በመሆኑ የአፍሪካን የአየር ለውጥ ጉባኤ የመምራት የሞራል ብቃት የለውም።

ይህ ገንዘብ መለስ ዜናዊን በመሳሰሉ የአፍሪካ አምባገነኖች እጅ የሚወድቅ ከሆነ ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ፣ አሁንም ገንዘቡ የአምባገነኖችን የስልጣን እድሜ ለማራዘሚያነት ሊውል ይችላል።

መለስ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እንዳገኘ አድርጎ በማስወራት የምእራብ አገሮችን ስሜት ለመያዝ መቻሉን የገለጹት ጸሀፊዋ፣  ነገር ግን የመለስ ሁለት አሀዝ እድገት በታዋቂ ኢኮኖሚስቶች አለመረጋገጡን እንዲያም በአለፉት 20 አመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው እድገት 5 በመቶ ሲሆን፣ አሀዙም ከአፍሪካ 6 በመቶ እድገት ጋር ሲተያይ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የእርዳታ ገንዘብ በተገቢው መንገድ ስራ ላይ መዋሉን የሚቆጣጠር ነጻ የሲቪክ ተቋማት በሌለሉበት ሁኔታ ገንዘብ መፍቀድ ማለት እነመለስ ዜናዊ እንዲዘርፉትና ገንዘባቸውን ወደ ውጭ እንዲልኩ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።

ጸሀፊዋ ለጋሽ አገሮች ገንዘቡን በትክክል የሚቆጣጠሩበትን ስርአት ሳይዘረጉ ገንዘቡ መለቀቅ እንደሌለበትም አስተያየታቸውን አስፍረዋል።