(ኢሳት ዜና–መስከረም 24/2010) ኢትዮጵያና ሱዳን በየሀገራቸው ገንዝብ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ከስምምነት ደረሱ።
ስምምነቱ ለሶስት አመት የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።
በተለያዩ የአለም ሀገራት የየሀገራቸው ገንዘብ የመጠቀም የንግድ ልውውጥ የማድረግ ስምምነት ይደረሳል።
እንዲህ አይነቱ ስምምነት በተለይ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ የሚገኝ ሀገር ጎረቤት ካለና በፖለቲካ ከሚስማማው ጋር የሚፈጽመው ስምምነት ነው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።
የኢትዮጵያ መንግስትም በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚዋዥቅ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ባይሆንም ስምምነቱን ግን መፈጸሙ ተሰምቷል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ዘላለም ተክሉ እንደሚሉት ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ስምምነት የሚያደርጉት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተቸገሩና አምባገነን የሆኑ መንግስታት ናቸው ይላሉ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው የየሀገራቸውን ገንዘብ የመጠቀም ስምምነት በተለይ ለሱዳን የሚጠቅም እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ዘላለም በቀጣይ በሁለቱም ሀገራት ባንኮችን የመክፈት እቅድ እንዳላቸውም ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ያደርገው ስምምነት የሀገሪቱን የወጭ ንግድ አንድ ከመቶ እንኳን አይሸፍንም ይላሉ ዶክተር ዘላለም።
በረዥም ጊዜ ደግሞ ሱዳን ከኢትዮጵያ ከምታገኘው የመሬት ጥቅም ጋር የተገናኘ እንደሆነና የፖለቲካ ስምምነት መሆኑንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከሱዳን መንግስት ጋር የምታደርገው ስምምነት በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት ወይም የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመቀነሱ ነገር ከአንድ ከመቶ በታች መሆኑንም ባለሙያው ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ለማግኘት በሚል ምክንያት የገንዘብ የመግዛት አቅምን ዝቅ እያደረገ ይገኛል።