የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ወደቀደመው አሰራር ተመልሻለሁ ሲል ተማሪዎቹ ግን የተቀየረ ነገር የለም አሉ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 24/2010)የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ወደቀደመው አሰራር ተመልሻለሁ ቢልም ተማሪዎቹ ምንም የተቀየረ ነገር እንደሌለ ገለጹ።

ከ1500 በላይ የ4ኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪዎች በውጤት አሰጣጥ ላይ በዩነቨርሲቲው የተጀመረውን አዲስ አሰራር በመቃወም ፈተናውን አንወስድም በማለታቸው ባለፈው ሰኞ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።

በባህርዳር በየአብያተክርስቲያናቱ የተጠለሉት ተማሪዎች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውንም ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ዩነቨርሲቲው ወደቀድሞው የውጤት አሰራር መመለሱን ቢገልጽም ወደግቢው ያመሩት አንዳንድ ተማሪዎች ግን ምንም የተለወጠ ነገር እንዳላዩ ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው አሰራሩን የቀየርኩት ከተማሪዎቹ ጋር ተወያይቼ ነው ቢልም ተማሪዎቹ ግን አይቀበሉትም። ሳናውቅ በድንገት የተወሰነ፡ ተማሪዎችን በገፍ ለማባረር የተወሰደ እርምጃ ይሉታል።

ፍጥጫው ከተጀመረ ወራት ተቆጥሯል። ተማሪዎቹ ጥያቄ አንስተው የዩኒቨርሲቲው አዲሱ አሰራር እንዲቀየር ያደረጉት ጫና ውጤት ሳያመጣ ቀረ።

አዲስ የውጤት አሰጣጥ ወደ ትግባር ልምምድ የሚገባ ተማሪ ፈተና በመውሰድ ከ50 በላይ ውጤት ማስመዝገብ አለበት የሚል ሲሆን ከቀደመው አሰራር የሚለይ ነበር።

ተማሪዎቹ አዲሱን የውጤት አሰጣጥ እንደማይቀበሉት በመግለጽ ትምህርት ያቆማሉ።

ዩኒቨርሲቲውም በጉዳዩ ላይ ተማሪዎቹን ከማወያየት ይልቅ የሃይል እርምጃን እንደመፍትሄ በመውሰድ ለተማሪዎቹ የሚሰጠው የምግብ አገልግሎት እንዲቆም ያደርጋል። ይህ እርምጃ የተማሪዎቹን ውሳኔ የሚያስቀይር አልሆነም።

በሳምንቱ መጀመሪያ ማለትም ባለፈው ሰኞ የአንድ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በቁጥር ከ1550 በላይ የሚሆኑት በሙሉ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የታጠቀ ሃይል በማሰማራት ተፈጻሚ ያደርጋል።

በዚህም ያልተበገሩት ተማሪዎቹ በባህርዳር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመጠለል በውሳኔያቸው በመጽናት ቀጠሉ።

ከሁለት ቀናት በኋላ ዩኒቨርስቲው አዲሱን አሰራር በመተው ወደቀደመው የውጤት አሰጣጥ መመለሱን ዛሬ ማስታወቁን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው አስፍረዋል።

ዩኒቨርስቲው ይህ ሁሉ የተማሪዎች መጉላላት ሳይከሰት ለጉዳዩ እልባት መስጠት እየቻለ አለማድረጉ እያነጋገረ ባለበት ሁኔታ መረጃውን የሰሙ የተወሰኑ ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲው ቢያመሩም ምንም የተለወጠ ነገር አላገኙም።

ዩኒቨርሲቲው አዲሱ አሰራር ከተማሪዎች ጋር በመወያየት የተደረገ እንደሆነ ዛሬ አስታውቆ ነበር። ተማሪዎቹ ተወያይተው ተስማምተው ቢሆኑ ኖሮ ትምህርት ለማቆም አይውስኑም ነበር የሚሉ ታዛቢዎች የዩኒቨርስቲው አስተዳደር በእልህ የሚወስዳቸው ውሳኔዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማስተጓጎል ባሻገር መንግስትን ለኪሳራ መዳረጉንም ይገልጻሉ።

ተማሪዎቹ እንደሚሉት ይህ ሁሉ ችግር ከመከሰቱ በፊት መወያየት ቢቻል ጥሩ ነበር፡ ዩንቨርሲቲው ግን ፍቃደኛ አልነበረም ይላሉ።

ዩኒቨርስቲው አሰራሩን ወደነበረበት እንደመለሰው ቢገልጽም ተማሪዎቹ እስከአሁን ወደግቢው አልተመለሱም።

የሚታይ የተለየ ነገር በሌለበት መመለስ አልቻልንም ያሉት ተማሪዎቹ አሁንም በየአብያተክርስቲያናቱ ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል። የሚበላ የሚጠጣ አሁንም ችግር ሆኖባቸዋል።