ቴዲ አፍሮ የኢሳት የ2009 የአመቱ ምርጥ ሰው በሚል ተመረጠ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 8/2010) ዝነኛው የሙዚቃ ሰው ቴዲ አፍሮ በከፍተኛ ድምጽ የኢሳት የ2009 የአመቱ ምርጥ ሰው በሚል ተመረጠ።

 

በኢሳት የ2010 የአዲስ አመት ፕሮግራም ላይ በተካሄደው ስነስርአት የኢሳት የሙሉጌታ ሉሌ መታሰቢያ የአመቱ ምርጥ ሰው ሽልማት ለድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ በኪነጥበብ ባለሙያዎች አማካኝነት ተበርክቷል።

 

በኢሳት የ2010 አዲስ አመትን አስመልክቶ በተካሄደው ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው ከነሀሴ 8 እስከ ጳጉሜ 4/2009 በኢሳት የስልክ መስመር፣ኢሜልና ፌስቡክ ድምጻቸውን ከሰጡ 2072 መራጮች ውስጥ ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን 1384 ድምጽ በማግኘት ቀዳሚ ሆኗል።

የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው ወጣቱ ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው በ2ተኛ ደረጃ ሲመረጥ በወህኒ የሚገኙት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር መረራ ጉዲና በሶስተኝነት ደረጃ የመራጮችን ድምጽ አግኝተዋል።

ዝነኛው የሙዚቃ ሰው ቴዲ አፍሮ በሕዝብ ድምጽ አንደኛ ሆኖ የተመረጠበትን የኢሳት የሙሉጌታ ሉሌን መታሰቢያ የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አበበ ገላውና የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሀብታሙ አያሌው ሽልማቱን አበርክተዋል።

የኢሳት የአመቱ ምርጥ ሰው የሙሉጌታ ሉሌን ሽልማት ባለፈው አመት በ2008 ያሸነፉት አትሌት ሌሊሳ ፈይሳና ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ መሆናቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሞና በሶማሌ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው ዕልቂት የሞቱትን ጨምሮ በአጠቃላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተገደሉትን ዜጎች በሕሊና ጸሎት በማሰብ የኢሳትን የአዲስ አመት ፕሮግራም ያስጀመሩት ጸሀፊ ተውኔት ጌታቸው አብዲ በእርግጥ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ምን አዲስ ነገር አለ? ምንስ ደስታ አለ?ሲሉ ጠይቀዋል።አመታትን እንቆጥራለን እንጂ ደስታ ከራቀን ቆይቷል ሲሉም የሚሰማቸውን ቁጭት ገልጸዋል።

አንጋፋው ደራሲ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር በክብር እንግድነት ተገኝተው በስራዎቻቸው ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አንጋፋው የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ የተጫወታቸውን ብዙዎቹን ሀገራዊ ዜማዎችን የደረሰትና የተለያዩ መጽሀፎችን ለንባብ ያበቁት ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

በኢትዮጵያ እየሆነ ባለው ነገር አልገረምም ያሉት ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ ሕወሃትን እንደ ኢትዮጵያዊ ቡድን ስለማይመለከቱት እንደሆነ ተናግረዋል።

አንጋፋዋ የባህል ሙዚቃ ንግስት ማሪቱ ለገሰ እንዲሁም ድምጻዊ ንግስት ሀዋዝ በዜማዎቻቸው ባደመቁት የኢሳት የአዲስ አመት ዝግጅት ታዋቂው ኮመዲያን ክበበው ገዳም በስራዎቹ ታዳሚዎችን አዝናንቷል።

በአሜሪካ ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያን ሕጻናት በባዕድ ሀገር ኢትዮጵያዊ ባህልን ጠብቆ ለማቆየት የጀመሩት ስራም ተመልካቾችን ያስደመመ እንደነበር ተመልክቷል።

ሕጻናቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ቋንቋዎች ሙዚቃ ሲጫወቱና ውዝዋዜ ሲያቀርቡ ታይተዋል።
በዝግጅታቸው ፉከራና ሽለላ ያቀረቡት ሕጻናት ለበአሉ ያዘጋጁትን ድራማም ተጫውተዋል።

የኢሳት አመታዊ ዝግጅት በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶችና ሌሎች አህጉራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ አስታውቋል።