የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታ የሚመለከተውን ረቂቅ የአሜሪካ ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ተጠየቀ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 8/2010) በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ያረቀቁትንና የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታ የሚመለከተውን ረቂቅ የአሜሪካ ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ጠየቁ።

አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን እልቂት በገንዘብ መደገፍዋን እንድታቆም ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።

ዛሬ ወደ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በመጓዝ ጥሪያቸውን ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን ሰልፈኞች በኢሬቻ አመታዊ በአል ላይ ያለቁ ኢትዮጵያውያንን ለማሰብ፣እንዲሁም የሰሞኑን ዕልቂት በማውገዝ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝ የረቀቀው ኤች አር 128 በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣና የፖለቲካ አፈና የተመለከተ በመሆኑ ይህንን ከ60 በላይ የኮንግረሱ አባላት የደገፉትን የአሜሪካ ምክር ቤት ተቀብሎ እንዲያጸድቀውም ጥሪ ለማቅረብ ሰልፈኞቹ ወደ አሜሪካ ምክር ቤት ካፒቶል አምርተዋል።