ታህሳስ 04 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አኝዋክ ጀስቲስ ካውንስልና ጥምረት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በጋራ ባወጡት መግለጫ የመለስ መንግሰት ልዩ ሀይል ከዲሰምበር 13እስከ 15 ባሉት ሶስት ቀናት ውስጥ 424 አኝዋኮችን ገድሏል።
ከዚያ በሁዋላ በነበሩት ተከታታይ አመታት በድምሩ 1500 አኝዋኮች መገደላቸውን መግለጫው አመልክቷል።
ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው የመለስ መንግስት በጊዜው በአኝዋኮች ላይ የወሰደው እርምጃ ምንክንያቱ የአካባቢውን መሬት፣ ውሀ፣ የተፈጥሮ ጋዝና ማእድናት ለመቆጣጠር ነው።
ዛሬ አኝዋኮችን የመግደያ ቀን ነው በሚል መፈክር ህጻናት፣ አሮጊቶች፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ሳይቀሩ ተጨፍጭፈዋል።
ዳውህ ማክ ጊል የተባለው ጋዜጠኛ በ2003 ባወጣው ሪፖርት ፣ አሜሪካ 113 አኝዋኮች መገደላቸውን ማጣራት እንደቻለች ገልጧል።
የመለስ መንግስት የዘር ማጥፋት ወነጀል ለመፈጸም ሙከራ ማድረጉን የአይን እማኞችን አነጋግሮ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።
በ2004 ሰርቫይቨርስ ራይትስ ኢንተርናሽናልና ጄኖሳይድ ወች የተባሉት አለማቀፍ ድርጅቶች የጸጥታው ምክር ቤትና የአፍሪካ ህብረት በጋምቤላ ክልል እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።
ሂውማን ራይትስ ወች በ2005 ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት 424 አኝዋኮችን መግደላቸውን፣ ከ400 በላይ ቤቶችን ማቃጠላቸውን፣ እንዲሁም በርካታ ንብረት መዝረፋቸውን ይፋ በማድረግ ጉዳዩ በሰው ልጆች ላይ በተፈጸመ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ገልጧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአለማቀፍ ማህበረሰብ የመጣበትን ግፊት ለማብረድ በሚመስል መልኩ የራሱን አጣሪ ኮሚቴ በማቋቋም ጭፍጨፋውን ለመሸፋፈን ሙከራ አድርጓል።
የመለስ መንግስት በጋምቤላ የሚገኘውን ሰፋፊ የእርሻ መሬት ለህንድ ባለሀብቶች እዚህ ግባ በማይባል ገንዘብ እየሸነሸነ በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ደግሞ የህወሀት ደጋፊዎች የክልሉን ደን በመጨፍጨፍና ከሰል በማክሰል ወደ ሱዳንና ጎረቤት አገሮች ይልካሉ።