“ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ባያስተካክልም፤ ሕዝቡ መብቱን ለማስከበር መነሳቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ተጠያቂ እኛና ሕዝቡ ሳንሆን፤ ራሱ ኢህአዴግ ነው የሚሆነው” ሲሉ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስጠነቀቁ

ታህሳስ 04 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዶክተር ነጋሶ ይህን ያሉት ሰሞኑን አንድነት ፓርቲን ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ይመሩ ዘንድ በአብላጫ ድምጽ መመረጣቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።
“የሰጣችሁኝ ኃላፊነት ከባድ እንደሆነ ሁላችንም የምንገነዘበው ነው” ያሉት የቀድሞው የ አገሪቱ ፕሬዚዳንት፤ “በተለይም የፖለቲካ ምሕዳሩ ባልተስተካከለበት ሁኔታ አንድን ፓርቲ መምራት በጣም ከባድ ነው”ብለዋል።
“ሆኖም ግን ፈቃደኝነቱ እንዲሁም የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ በመሆን በቆራጥነት ለመታገል መነሳሳት ካለ፤ የትኛውንም ችግር መወጣት ይቻላል፡፡ ኃላፊነቱን ለመቀበልም ፈቃደኝነቴን ስገልጽ፤ እነዚህ ባህሪያት እንዳሉኝ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ለትግሉ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል-አዲሱ የ አንድነት ሊቀ-መንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ።
ዶክተር ነጋሶ አክለውም ፦”ከዚህም በተጨማሪ ከድርጅቱ አባላት፤ከደጋፊዎችና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አገኛለሁ የሚል ጽኑ እምነት ስላለኝ፤ ኃላፊነቴንና ግዴታየን በጋራ እንወጣለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ”ብለዋል።
“መንግሥት፤ የፓርቲያችን አመራር አባላት የሆኑትን አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ ናትናኤል መኮንንን ጨምሮ ሌሎች ንፁሃን ዜጐችን በአሸባሪነት ሽፋን በማሰር ሠላማዊ እንቅስቃሴን ለማፈን የሚያደርገው ሩጫና የፓርቲያችንን መልካም ስምና ዝናን ለማበላሸት በማከናወን ላይ ያለው ተግባርም መገታት ይኖርበታል” ያሉት ዶክተር ነጋሶ ፤ በ እስር ላይ ያሉት አባሎቻችን እንዲፈቱና ፓርቲያችን ወደፊት እንዲራመድ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን ብለዋል።
“ለ ኢህአዴግ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ…” በማለትም የአንድነት ፓርቲ ፍላጎት ህገ-መንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ እንጂ የገንዘብና የንብረት ፍርፋሪ መቃረም እንዳልሆነ ሊቀመንበሩ ዶክተር ነጋሶ አስገንዝበዋል።
“ጥያቄያችን ኢህአዴግ ከፓርላማ ከያዛቸው ወንበሮች አንድና ሁለት እንዲሰጠን ወይም ስልጣን እንዲያካፍለን አይደለም።እኛ የምንጠይቀው የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያስተካክል ብቻ ነው።እያልን ያለነው፤ ህዝቡ በነፃና በፍትሀዊ ምርጫ የሚመራውን ፓርቲ የሚመርጥበት ሁኔታ ይመቻች ነው” ብለዋል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ካላስተካከለ፤ ህዝቡ በራሱ ጊዜ መብቱን ለማስከበር መነሳቱ አይቀርም” ያሉት ዶክተር ነጋሶ፤ “ያኔ… ተጠያቂው እኛና ህዝቡ ሳንሆን፤ ራሱ ኢህአዴግ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።