(ኢሳት ዜና –ጳጉሜ 1/2009)የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ) ከስልጣን እንዲለቁ ከተለያዩ ወገኖች እየተጠየቁ ነው።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አብድልከሪም ሼህ ሙሴን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ለሚመራው መንግስት አሳልፈው የሰጡት ፕሬዝዳንቱ ከሀገር ውስጥና ከባህርማዶ በሶማሊያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
በሶማሊያ የሚሰራጩ የመገናኛ ብዙሃንም ዘመቻ ከፍተዋል።
የሶማሊያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላትና ታላላቅ ሰዎች ፕሬዝዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
ተቃውሞ በዚሁ ከቀጠለ ፋርማጆ ስልጣናቸውን በቅርቡ የመልቀቃቸው ነገር የማይቀር ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ሞቃዲሾ የተወለዱት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ሶማሊያ ወደ ሀገር አልባነት ከመቀየሯ በፊትም ፖለቲካ ውስጥ ነበሩ።
በአሜሪካ የሶማሊያ ኤምባሲ በአንደኛ ደረጃ ጸሃፊነት መስራታቸው ይታወቃል። የምዕራቡን ዓለም ፖለቲካ በጠዋቱ የተዋሃዱት ፋርማጆ ወደ ላይኛው የስልጣን ደረጃ ለመምጣት ጊዜ ወስዶባቸዋል።
የዚያድባሬ ስርዓት አክትሞ ሶማሊያ እንደሀገር መቆም ካቃታት 1991 እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ጀምሮ በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች አገልግለዋል።
በምዕራቡ ዓለም ጣልቃ ገብነት ተቃውሟቸው የሚታወቁት ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ መሀመድ በቅጽል ስማቸው ፋርማጆ ነው በሰፊው የሚታወቁት።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የሞቃዲሾ ቤተመንግስት ቅርብ እንደሚሆንላቸው በግልጽ መታወቅ ጀመረ።
በተለይም በሶማሊያ የውጭ ሀገራትን ጣልቃ ገብነት አጥብቀው የሚያወግዙ መሆናቸው በሶማሊያውያን ዘንድ የተለየ ቦታ እንዲሰጣቸው አድርጓል። በኋላም ወደ ፕሬዝዳንትነቱ ያመራቸው መንገድም ይሕው ጣልቃ ገብነት ላይ ያላቸው የጸና አቋም እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ምንም እንኳን የተበታተነችውን ሶማሊያ ወደ አንድ ለማምጣት ባይችሉም፣ የአልሸባብንም ሆነ የሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ባያስቆሙም ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ ማድረጋቸው በአዎንታዊነት የሚጠቀስላቸው ስኬት ሆኗል።
በተለይም በሰላም አስከባሪነት ስም በሀገራቸው ምድር የሰፈረው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው ሰራዊት ለፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሚቀበሉት ነገር አይደለም።
ብዙዎች እሳቸው ወደስልጣን ሲመጡ በህወሀት የሚመራው ጦር ከሶማሊያ ምድር እንዲለቅ ያደርጋሉ የሚል ግምት እንደነበራቸው ዘገባዎች ያመለክታሉ። በዚህም ምክንያት ለህወሀት መንግስት የማይመቹ ተብለው የሚጠቀሱ ፕሬዝዳንት ናቸው ።
ይህም ከህዝባቸው ያስገኘላቸው ድጋፍ ቀላል የሚባል አይደለም። አቶ ጀማል ዲሪዬ ካሊፍ የሶማሌ ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ ሰብሳቢ እንደሚሉት ፋርማጆ የተመረጡበትን ቃላቸውን አፍርሰዋል።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ አንድ ዓመት ያልደፈነው የፕሬዝዳንትነት ወንበራቸው ከወዲሁ መነቃነቅ ጀምሯል። ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ለሚመራው መንግስት የዋሉት ውለታ ዋጋ እያስከፈላቸው ነው።
ከ1ሳምንት በፊት የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር አመራር አባል የሆኑትን አብዱልከሪም ሼህ ሙሴን በቁጥጥር ስር አውለው የነበሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሀምድ አብዱላሂ ሞሀመድ የቀደመ አቋምቸውን ወደ ጎን አድርገው ለህወሀት መንግስት አሳልፈው መስጠታቸው መንግስታቸውን ያልተጠበቀ ቀውስ ውስጥ ከቶታል።
በሶስት የሶማሊያ ከተሞች ህዝቡ አደባባይ በመውጣት በመንግስታቸው እርምጃ መቆጣታቸውን የገለጹ ሲሆን ‘’እንዴት ለጠላት መንግስት ተላልፈው ይሰጣሉ’’ የሚለው ድምጽ ጎልቶ መውጣት ጀመሯል።
የሀገሪቱን ህገመንግስትም ሆነ ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ለህወሀት መንግስት አሳልፈው የሰጡበት ድርጊት በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ከሶማሊያውያን ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ እንዲገጥማቸው አድርጓል።
በሶማሊኛ ቋንቋ የሚተላለፉ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ይሕው የአብዱልከሪም ሼህ ሙሴ ለህወሀት መንግስት ተላልፎ መሰጠት ሆኗል።
የሶማሊያ ህግ አውጪዎች ድርጊቱ የተፈጸመው በህገወጥ መንገድ በመሆኑ ፕሬዝዳንቱ በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸው የተገለጸ ሲሆን ግፊቱ ከየአቅጣጫው መጨመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፋርማጆ ላይ ህዝባቸው ተነስቷል። ለህወሀት መንግስት አሳልፈው በሰጡት የኦጋዴን አመራር ላይ የተቀሰቀሰባቸው ተቃውሞ ወንበራቸውን ሊያሳጣቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ፋርማጆ ከሁለት አንድ ያጣ ሆነዋልም እየተባለ ነው። ከህወሀት መንግስት ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት ባልተሻሻለበት ሁኔታ ከህዝባቸው መላተማቸው መጪውን ጊዜ አጣብቂኝ አድርጎባቸዋል።
አቶ ጀማል ዲሪዬ እንደሚሉት ፋርማጆ በህዝባቸው ግፊት ከስልጣን መውረዳቸው ሶማሊያውያን ቤተመንግስት የሚቀመጥ መሪያቸው ለህወሀት መንግስት ወዳጅ አለመሆኑን የሚያሳይ መሆን እንዳለበት የሚያረጋግጥ ይሆናል።