በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ባለው ስታዲየም በደረሰ አደጋ 7 ሰዎች ሲሞቱ ከ30 በላይ ቆሰሉ

(ኢሳት ዜና –ጳጉሜ 1/2009)በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ባለውና በቻይና ኩባንያ በመሰራት ላይ በሚገኘው ስታዲየም በደረሰ የእሳት አደጋ 7 ሰዎች መሞታቸውና ከ30 በላይ መቁሰላቸው ከተደበቀ ከአንድ ወር በኋላ ተጋለጠ።

የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙናንን ማለትም እንደ አሶሼትድ ፕረስ፣ ኢቢሲ ኒውስና የመሳሰሉትን ትኩረት የሳበው ይህ አደጋ የተጋለጠው ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ለአዲስ ሽታንዳርድ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ገርጂ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ በመገንባት ላይ ባለው አደይ አበባ ስታዲየም በሰራተኞች መኖሪያ ውስጥ ሲሊንደር ፈንድቶ ጉዳት የደረሰው እንደ አውሮፓውያኑ ነሀሴ 8/2017 እንደሆነም ታውቋል።

በአደጋውም 7 ኢትዮጵያውያን ሲሞቱ 32 የተጎዱበትን ይህን አደጋ የቻይና ኩባንያ የስራ ሃላፊዎች ያረጋገጡ ሲሆን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

800 ኢትዮጵያውያንና 200 ያህል ቻይናውያን ሰራተኞች በሚገኙበት አደይ አበባ ስታዲየም የሰራተኞች መኖሪያ ቤት ውስጥ ሲሊንደሩ የፈነዳው በተጠቀሰው ቀን ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ ሲሆን ከፊሉ ሰራተኛ ከተኛና ሌሎቹ ደግሞ እራት ለመብላት በመዘጋጀት እንዳሉ አደጋው ተከስቷል።

ወደ 2 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ስታዲየም ስራ የሚያከናውነው የቻይናው ስቴት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለሟች ቤተሰቦች ካሳ ለእያንዳንዳቸው 15 ሺህ ብር ካሳ ለመክፈል በማግባባት ላይ መሆኑ ታውቋል።

አካላቸው ለቆሰለው ደግሞ የመደበው 3 ሺህ ብር እንደሆነም ከአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ መረዳት ተችሏል።
የሟች ቤተሰቦች በሃሳቡ አለመስማማታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

ወንደሰን ደመቀ፣ኡመር አብደላና ያለው ጸሃይ በአደጋው እጅና እግራቸው ተቃጥሏል።በሚኒሊክ ሆስፒታልም እርዳታ ተደርጎላቸው ከወጡ በኋላ ለአዲስ ስታንዳርድ በሰጡት መግለጫ 7ቱ ባልደረቦቻቸው መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
ጉተማ መሹ፣ሹፍሪ አብዱራህማን፣አልይ መሀመድ፣ከዲሮ ሚዳሶና ዲታ ገለቶ ከሻሸመኔ አዲስ አበባ ለስራ መተው ሕይወታቸውን ሲያጡ ብርሃኑ በላይና መንግስቱ ደበሽ ከወሎ የመጡ ናቸው።የ7ቱም አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መላኩም ታውቋል።

የዛሬ 77 አመት በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተሰራውና 35 ሺ ሕዝብ የሚይዘውን የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለመተካት በመገንባት ላይ ያለው የአደይ አበባ ስታዲየም 60 ሺህ ያህል ሰዎችን መያዝ የሚችል እንደሆነም መረዳት ተችሏል።