(ኢሳት ዜና–ነሀሴ 24/2009)ለ5 ቀናት ዶፍ ዝናብ የወረደባትና በ20 ትሪሊዮን ጋሎን ያህል ውሃ የተጥለቀለቀችው የአሜካዋ ሒዩስተን ከተማ በመልሶ ግንባታው ሒደት የኮንስትራክሽን ሰራተኞች እጥረት ሊገጥማት ይችላል ተባለ።
ዝናቡም ከሂውስተን ወደ ሉዚያና መሻገሩም ተመልክቷል።
በዚህ እጅግ ከፍተኛ በሆነው አደጋ በጎርፍ የተወሰዱ 6 የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ 20 ሰዎች መሞታቸው ይፋ ሆኗል።
እድሜያቸው ከ6 እስከ 16 አመት የሆነ 4 ልጆች በ80ዎቹ የእድሜ ክልል ከሚገኙት አያቶቻቸው ጋር የተሳፈሩበት ቫን መኪና እሁድ እለት በጎርፍ በመወሰዱ የደረሱበት አልታወቀም በሕይወት የመገኘታቸው ጉዳይም አጠራጣሪ ሆኗል።
በሂውስተን አደጋ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች ብዙዎቹ ከአደጋው አካባቢ ለመሸሽ በሚንቀሳቀሱበት ወይንም በተለመደው ተግባራቸው በጉዞ ላይ ባሉበት በመኪና ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ ተመልክቷል።
እስከ ባለፈው ሰኞ ከሞቱት 66 በመቶው በመኪና ጉዞ ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉ ሲገለጽ በእግራቸው እየተጓዙ፣አሳ እያሰገሩና እየተጫወቱ ለአደጋ የተጋለጡ መኖራቸው ተዘርዝሯል።
በዩኤስ አሜሪካ ከሚገኙ 400 ያህል ከተሞች በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውና ኒዮርክን፣ሎስአንጀለስና ቺካጎን የምትከተለው ሂውስተን 2 ሚሊየን 3 መቶ ሺ ያህል ሕዝብ ይኖርባታል።
በአካባቢው ያሉትን ከተሞች ጨምሮ በዙሪያዋ 6 ሚሊየን ያህል ሰዎች ይገኛሉ።
ከርእሰ መዲናዋ ዋሽንግተን በ1ሺ 408 ማይል ወይንም በ2 ሺ 271 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘውና የቴክሳስ ግዛት አካል የሆነችው ሒውስተን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1836 ነሀሴ ወር መቆርቆሯ ይታወቃል።
በ181 አመት እድሜዋ እጅግ ከፍተኛ የተባለውንና የየብስ መገናኛዋን ወደ ባህር መጓጓዣ የለወጠ 20 ትሪሊየን ጋሎን ውሃ በቀናት አስተናግዳለች።
በአመት ውስጥ አግኝታ የማታውቀውን የዝናብ መጠን በቀናት 50 ኢንች ያህል ውሃ ወርዶባታል።
በታሪክ ከፍተኛ ተብሎ የሚጠቀሰው ዝናብ የዛሬ 51 አመት በደቡብ ኢንዲያን ኦሽን ላሪዮኒያን ደሴት ላይ የጣለው ሲሆን በ24 ሰአት 71 ነጥብ 8 ኢንች ዝናብ ተመዝግቧል።
ስፓኒሾች ከፍተኛውን ቁጥር በሚይዙበት ሂውስተን ከሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች አንጻር የቤት ኪራይ ዋጋ በአማካኝ በ21 በመቶ የቀነሰና በኑሮ ወጪም ሲታይ ከአጠቃላዩ በአማካኝ በ9 በመቶ ዝቅ ያለበት ለኑሮ የማትጎረብጥ ሀብት የተከማቸባት ከተማ ነች።
ሀገራዊ ምርቷ ከአሜሪካ ተነጥሎ ከአለም ሀገራት ጋር ቢወዳደር እሷን የሚበልጧት 20 ሀገራት ብቻ ናቸው።
የአለማችን ግዙፍ የጤና ተቋም ቴክሳስ ሜዲካል ሴንተር የሚገኝባት ሲሆን በቢሊየን ዶላሮች የሚንቀሳቀሰው ይህ ቁጥር አንድ የጤና ማእከል 52 ሺህ ያህል ሰራተኞች የሚገኙበትና በአመት በ5 ሚሊየን ያህል ህሙማን የሚጎበኝ እንደሆነም ታውቋል።
ቴክሳስ የአለማችን የሃይል ማመንጫ ማእከል ተብላም ትጠቀሳለች።
ከ5 ሺህ በላይ የሃይል ማመንጫዎች ያሉባት፣በአሜሪካ ትልቁ ወደብ የሚገኝባትና ከፍተኛ ሀገራዊ ምርት የተከማቸባት ከተማ ነች።
የኢትዮጵያውያን እንዲሁም የአለማችን ቅርስ የሆነችው ሉሲ የዛሬ 10 አመት ወደ አሜሪካ በተጓዘችበት ወቅት በሂውስተን ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየም እንደ አውሮፓውያኑ ከሚያዚያ 20/2007 ጀምሮ በጎብኝዎችና በነዋሪዎች መጎብኘቷ ይታወሳል።
3 ነጥብ 2 ሚሊየን አመት እድሜ ያስቆጠረችው ሉሲ ወደ ሀገሯ ከተመለሰች ጥቂት አመታትን አስቆጥራለች።