የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ለማስወገድ መታገል ይኖርበታል ተባለ

(ኢሳት ዜና –ነሀሴ 24/2009) ኢትዮጵያ አደገኛ በሆነ አቅጣጫ እየተወሰደች በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ለማስወገድ መታገል ይኖርበታል ሲል የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ለም መሬቶችን ለሱዳን ለ10ዓመታት በውሰት ለመስጠት በድብቅ ከስምምነት መደረሱን በመጥቀስ ጥሪ ያደረገው የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ፡ የህወሀት መንግስት የጥፋት ግስጋሴ በአስቸኳይ ካልተገታ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው ብሏል።

የታላቋን ትግራይ ካርታ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃን በማሳየት ህዝቡ እንዲለማመደው እየተደረገ መሆኑና፡ ጎንደርን ለሶስት የመሸንሸኑ እርምጃ የዚሁ የታላቋ ትግራይ ምስረታ አካል ነው ብሏል የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ።

ኢሳት የመረጃ ምንጮቹን ጠቅሶ ትላንት ይፋ እንዳደረገው በሕወሃት የሚመራው መንግስት በጎንደር በኩል የሚገኝን አዋሳኝ የኢትዮጵያ ድንበር ለሱዳን ለ10 አመታት በውሰት ለመስጠት በድብቅ ተስማምቷል።
የትግራይን መስፋፋት ዕውን ለማድረግ ከተቀመጡት ዕቅዶች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለትና ለሱዳን የሚሰጠውን መሬት በተመለከተ እንደተገለጸው የቤንሻንጉልና የአማራ ተወካዮች በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ከተደራዳሪነት እንዲወጡ ተደርገዋል።
የትግራይ ክልል ሰዎች ብቻ በድንበሩ ጉዳይ ላይ በሚስጥር እየተወያዩ መሆኑንም የኢሳት ምንጮች መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሜቴ በተለይ ለኢሳት እንደገለጸው ለሱዳን ለ10ዓመት በውሰት ሊሰጥ በድብቅ ስምምነት የተደረገበት ምክንያት አለ።
ከ10ዓመት በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ሊጠቃለሉ በድብቅ ካርታ ውስጥ ከተካተቱት መሬቶች ውስጥ አሁን ለሱዳን በውሰት የሚሰጡት ይገኙበታል ያላሉ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዓለሙ ያይኔ።

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ታላቋን ትግራይ የመመስረት ህልሙ የሚሳካ አይደለም የሚሉ ወገኖች አቋማቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርጉ ክስተቶች እየተደጋገሙ መምጣታቸውን ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

ከኤርትራ ጋር ደም ያፋሰሰ የዕልቂት ጦርነት የታላቋን ትግራይ እቅድ ያከሸፈ መሆኑን የሚገልጹ ወገኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀወሃት መንግስት ከሱዳን ጋር በድብቅ የሚያደርጋቸው ስምምነቶች፡ የትግራይ ክልል በኢንዱስትሪና በዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ከሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ ልቃ እንድትሄድ በመንግስት በኩል ልዩና አድሎአዊ ድጋፍ እንዲደረግላት መወሰኑ፣ የሀገር መከላከያና የቴሌኮምኒኬሽን ቁልፍ ተቋማት ወደ ትግራይ ክልል መወሰዳቸውንና ሌሎች በአደባባይና በጀርባ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን መነሻ በማድረግ የታላቋ ትግራይ ምስረታ ሂደት ላይ ያለ መሆኑን የሚገልጹ ወገኖች እየበረከቱ መጥተዋል።

በመንግስት ቴሌቪዥን በድብቅ የተቀረጸውን የታላቋን ትግራይ ካርታ በተደጋጋሚ በማሳየት ህዝቡ እንዲለምደው የተደረገበት ያለምክንያት አይደለም የሚሉት የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዓለሙ ያይኔ፡ ህወሀት ወደፊት ሊያመጧት ያሰቧትን ኢትዮጵያ ከወዲሁ እያለማምዱን ነው። ህወሀቶች እያሰቡት ያለው ነገር በጣም አደገኛም ነው ይላሉ።

የታላቋ ትግራይ ምስረታ አካል የሆነው አንዱም የአማራው መሬት በፊት ለፊትና በእጅ አዙር የመንጠቅ እርምጃ ሲሆን የቅማንት ህዝብ የራሱ አስተዳደር ይኑረው የሚለው በህወሀት የተቀመረው መርዛማ ህዝበ ውሳኔ ሊደረግበት ጥቂት ቀናት ቀርተውታል ያሉት አቶ ዓለሙ ያይኔ ሰሞኑን ጎንደርን ለሶስት የመክፈሉም ውሳኔ የዚሁ የታላቋ ትግራይ አጀንዳ ማስፈጸሚያ እርምጃ እንደሆነ መጠራጠሩ የዋህነት እንደሆነም በማስረገጥ ይገልጻሉ።
የዳሽን ተራራንና የአባይ ግድብን በትግራይ ክልል ስር እንደሆኑ ለትግራይ ተማሪዎች በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲማሩት መደረጉና ላሊበላን በትግራይ ክልል ውስጥ አድርጎ የተለፈፈውን ማስታወቂያ የሚጠቅሱት አቶ ዓለሙ ያይኔ ድብቁን አጀንዳ ቀስ በቀስ ግልጽ ሆኖ ወደ አደባባይ እስኪወጣ ድረስ በዚህ መልኩ ማለማመዱ በህወሀት ዘንድ ተመራጭ ሆኖ የተገኘ ይመስለኛል ሲሉም ይገልጻሉ። ለዚህም 24 ሰዓት እየሰሩበት ነው።

ለአዲሱ ዓመት መቀበያ የ10ቀናት ድግስ ተዘጋጅቷል።
ህዝብን የሚያደነዝዙ በዓላትና ድግሶች በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በሚመራው መንግስት ዓይነተኛ የማስቀየሻ ስትራቴጂዎች ሆነው ይከናወናሉ።
ከጀርባ ሀገር እያፈረሰ ከፊት የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያንጸባርቁ የበዓል ዝግጅቶችን በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ የሚያከበረው የህወሀት ስርዓት ካልተወገደ በቀር የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ አሳሳቢ እንደሆነ የሚስማሙት ጥቂቶች አይደሉም።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ አቶ ዓለሙ ያይኔ ህዝቡ በበዓላትና ድግሶች መደንዘዙን አቁሞ የህወሀትን ድብቅ ሴር ማክሸፍ አለበት ይላሉ።