(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 24/2009) ለ25 አመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አካባቢያዊ ስሜትን ሲያቀነቅን የነበረው ስልጣን ላይ ያለው ቡድን
ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መጪውን የኢትዮጵያ አዲስ አመት ከወትሮው በተለየ አከብራለሁ ማለቱ ተሰማ።
ከነሐሴ 24 እስከ ጳጉሜ 5/2009 በተዘረጋለት መርሃ ግብር መሰረት የሚከበረው በአል የመንግስት ሰራተኞች የባህል ልብስ እንዲለብሱም ያስገድዳል።
ለ10 ቀናት የሚከበረው ይሄ በአል በየቀኑ የሚቀያየሩ መሪ ቃሎችንም አስቀምጧል።
ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መጪውን የኢትዮጵያ አዲስ አመት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለማክበር በሚል በወጣው መርሃ ግብር የሃይማኖት አባቶች በሆስፒታል የሚገኙ ህሙማንንና በወህኒ የሚገኙ እስረኞችን እንዲጎበኙ መርሃ ግብሩ ያዛል።
የፌደራልና የመከላከያ እግረኛ ማርሽ ባንድ እንዲሁም የአየር ሃይል ሄሊኮፕተሮች ሙዚቃ በማሰማትና ወረቀት በመበተን እንደሚሳተፉም በመርሃ ግብሩ ተቀምጧል።
መስከረም 1/2010 የሚወለዱ ህጻናት ታሪካዊና እድለኛ መሆናቸውን የሚገልጽ ፖስት ካርድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚበረከትላቸውም ተገልጿል።
ሕጻናቱ እድለኛ ተብለው ስለሚሰየሙበት ምክንያት ግን የተባለ ነገር የለም።
የሙዚቃ ፕሮግራሞችን ጨምሮ ልዩ ልዩ መዝናኛዎች በመርሃ ግብሩ የተካተቱ ሲሆን ይህንን ለማስፈጸም ሸዋፈራሁና ሰራዊት መልቲ ሚዲያ የተባሉ የማስታወቂያ ድርጅቶች ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።
ሕጻናት ቤተመንግስት ተገኝተው ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ፎቶግራፍ የሚነሱ ሲሆን አቶ ሃይለማርያም ለሕጻናቱ መጽሀፍ እንዲያነቡላቸው ፕሮግራም ተቀርጿል።
ለጳጉሜ 2/2009 የተቀረጸው መርሃ ግብር ደግሞ የመከላከያና የፖሊስ አባላት እርስ በርስ ወታደራዊ ሰላምታ እንዲለዋወጡ የሚያሳስብ ነው።
ኢትዮጵያውያንም ከወትሮው በተለየ መልኩ በፍቅርና በአክብሮት ሰላምታ እንዲለዋወጡ ያዛል።
በመላው ኢትዮጵያ በየመስሪያ ቤቱ፣በየመንገዱ፣በየአድባራቱ፣በውጭ ሀገር ባሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ቀጠሮ የተያዘው ጳጉሜ 3 መሆኑ ታውቋል።
በኩራት ከፍ ብሎ መውለብለብ በሚል የተጠቀሰው እንዴት እንደሚፈጸም ግን ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
ወትሮውንም ባንዲራ ሲውለበለብባቸው በነበረ ኤምባሲዎችም በተለየ ሁኔታ እንዴት ሊውለበለብ እንደሚችል ግልጽ አልሆነም።
በመርሃ ግብሩ መሰረት የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ለአምስት ደቂቃ በመላ ሀገሪቱ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ይቆማል።በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተመሳሳይ ስራ መስራትም አይቻልም።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ከብሔራዊ መዝሙር ውጪ ምንም የተለየ ድምጽ እንዳይሰማ መከልከሉንም ባለ 12 ገጹ መርሃ ግብር ይዘረዝራል።
በስራ ቦታም ይሁን በመዝናኛ ስፍራ፣ በእምነት ተቋማትም ይሁን በሌላ ቦታ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የባህል ልብስ መልበስን ያሚያሳስበው የ2010 አዲስ አመት መቀበያ ፕሮግራም የሚመሩና የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችም ነጭ ልብስ እንዲለብሱም ያዛል።
በቀድሞው ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ግን ሀበሻ ልብስ መልበስም ሆነ ማህተምን ፊት ለፊት እይሳዩ ዜናንም ሆነ ፕሮግራምን መምራት የሚከለክል ህግ ተቀምጦ እንደነበር በግልጽ የሚታወቅ ነው።
ነጫጭ ባንዲራዎችን ማውለብለብ ብሎም ነጫጭ ርግቦችን መልቀቅን የሚጨምረው ይሄ የ10 ቀን ፕሮግራም ጳጉሜ 5/2009 እኩለ ለሊት ላይ በርጭት ተኩስ እንደሚጠናቀቅ ተመልክቷል።
25 አመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አካባቢያዊ ስሜትን ሲያቀነቅን የነበረው ስልጣን ላይ ያለው ቡድን በሀገሪቱ የአድሎ ስርአት በመዘርጋት በኢትዮጵያውያን መካከል ልዩነትን ሲያሰፋ ከቆየ በኋላ አሁን የኢትዮጵያ አጀንዳ አጥልቆ የመጣበት ምክንያት በግልጽ አልታወቀም።
ስርአቱ ውስጣዊ ቀውሱን ለመሸፈን የሚያደርገው ሽርጉድ ነው ሲሉ ታዛቢዎች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው።