(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 22/2009) ከጊኒ ህዝብ በዘረፉት ሀብት በአሜሪካ ተቀማጥለው ሲኖሩ የነበሩት አንድ የጊኒ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣን በአሜሪካ ፍርድ ቤት እስራት ተበየነባቸው።
ወንጀል ሆኖ የቀረበባቸው ክስ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ዘርፈዋል በተባለው ሐብት ነው።
አሜሪካ የሌቦች መደበቂያ እንደማትሆንም የአሜሪካ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።
ከኢትዮጵያ ሀብት የዘረፉ የመንግስት ባለስልጣናት በዘመዶቻቸውና በራሳቸው ስም ወደ አሜሪካ ያሸሹትን ገንዘብ ለማስመለስ ኢትዮጵያውያን ለሚያደርጉት ጥረት በጊኒው ባላስልጣን ላይ አሜሪካ የወሰደቸው ርምጃ አበረታች ሆኖ መገኘቱንም መረዳት ተችሏል።
የ50 አመቱ የቀድሞ የጊኒ የማእድንና የጂኦሎጂ ሚኒስትር መሀምድ ጣይም በጊኒ ሕዝብ ኪሳራ ሰናንጎል ከተባለ ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር ባደረጉት የሚስጥር ስምምነት ባገኙት ገንዘብ ልጆቻቸውን በኒዮርክ ማንሃታን የግል ትምህርት ቤት እያስተማሩ መሆናቸው ታውቋል።
በዚሁ በኒዮርክ ከተማ በደች ካውንቲ የ3 ሚሊየን 750 ሺ የአሜሪካን ዶላር መሬትና ቤት መግዛታቸውም ተመልክቷል።
ባለስልጣኑ ከቻይናው ኩባንያ ካገኙት 8 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር፣3 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ዶላር ወደ አሜሪካ መሸጋገሩም በምርመራ ተረጋግጧል።
ግለሰቡ ገንዘቡን ከቻይናው ኩባንያ ያገኙት ከ2009 እስከ 2011 ባሉት ሁለት አመታት ብቻ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
በጊኒ ህዝብ ኪሳራ ራሳቸውን ያበለጸጉትና ገንዘቡንም በማሸሽ በዩ ኤስ አሜሪካ በተንደላቀቀ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ የነበሩት መሀምድ ጣይም በኒዮርክ ፍርድ ቤት የ7 አመታት እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን በውሳኔውም መሰረት ወህኒ ወርደዋል።
በጊኒው ባለስልጣን ላይ የተላለፈው የፍርድ ቤት ውሳኔ ለሌሎች ሌቦችም በቂ መልእክት ያስተላልፋል ያሉት የአሜሪካ ተጠባባቂ ረዳት ጠቅላይ አቃቢ ህግ ኬንት ብላንኮ የአሜሪካን የፋይናንስ መዋቅር የሌቦች ገንዘብ መሻገሪያና መሸሸጊያ እንደማይሆንም አሳስበዋል።
የአሜሪካው የፌዴራል የምርመራ ቢሮ ኤፍ ቢ አይ ጭምር ባለስልጣኑን ለፍርድ በማቅረቡ ረገድ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ተመልክቷል።
በጊኒው ባለስልጣን ላይ የተወሰደው ይህ የቅጣት ውሳኔ ሀብታቸውን በተመለከተም በሚመለከተው አካል ቀጣይ ርምጃ እንደሚኖር ይጠበቃል።
ይህ የአሜሪካ መንግስት ርምጃ ወደ አሜሪካ ሀብት በማሸሽ ላይ በሚገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ላይ ግልጽ መልእክት አስተላልፏል።
በራሳቸው ስም እንዲሁም በዘመዶቻቸው ስም ቤትና ሱቅ በመግዛት እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ በማስቀመጥ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መኖራቸውንም መረዳት ተችሏል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት አሜሪካዊ ዜግነት በወሰዱ ልጆቻቸው እንዲሁም ቤተሰብ የሌላቸውም የመኖሪያ ፈቃድ በመውሰድ ላይ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
ግማሽ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላርና ከዚያ በላይ ያላቸው ግለሰቦች በኢንቨስተር ስም የአሜሪካንን የመኖሪያ ፈቃድ መውሰድ እንደሚችሉ ይታወቃል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ መጠኑ ከአንድ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከፍ እንደሚልም ይታወቃል።