ገዢው ፓርቲ በነጋዴዎች እየቀረበ ያለውን ጥያቄ ወደ ጎን በማለት “የበቀል እርምጃ” እየወሰደ ነው ሲሉ ነጋዴዎች ተናገሩ

ሐምሌ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፉት 2 ሳምንታት ሲካሄድ የቆየውን የነጋዴዎች አድማ ተከትሎ፣ ገዢው ፓርቲ “ችግሩን በውይይት እፈታለሁ” በማለት በየስብሰባዎች ቃል እየገባ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ለማግባባት ሲሞክር ከቆየ በሁዋላ ወደ በቀል እርምጃ መግባቱን ነጋዴዎች ይገልጻሉ።
የሞጣ ከተማ ባለስልጣናት ሰሞኑን በተከታታይ ባደረጉት ስብሰባዎች ለነጋዴዎች ጥያቄ አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጡ ሲገልጹ ቢቆዩም፣ ዛሬ ለነጋዴዎች ያላቸውን ንቀትና “ ምንም አታመጡም ለማለት” የግብር ተመኑን በንግድ ድርጀቶች በርና መስኮቶች ላይ ሲለጥፉ ማርፈዳቸውን ነጋዴዎች ተናግረዋል።
ነጋዴዎች በያዙት አቋም በምጽናት ለ6ኛ ቀን አድማውን እያካሄዱ ሲሆን፣ የሌሎች አካባቢ ነጋዴዎችም እንዲተባባሩዋቸው ጠይቀዋል። “በአንድነት ከተነሳን ነጣጥሎ ሊያጠቃን አይችልም” የሚሉት ነጋዴዎች ፣ በምስራቅ ጎጃም የተለያዩ ወረዳዎች የሚታየው የነጋዴዎች አንድነት በሌሎችም አካባቢዎች ሊደገም እንደሚገባ ይመክራሉ።
በሸበል በረንታ እንደተደረገው ሁሉ ዛሬ ከሰአት በሁዋላ በሞጣም አንዳንድ ነጋዴዎች ተይዘው እየታሰሩ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በምስራቅ ሃረርጌ በዳዳር፣ እንዲሁም በአለም ገናም ነጋዴዎች አድማ እየተካሄደ ነው። በዳዳር ትናንት ወረቀቶች መለጠፋቸውን ተከትሎ የኦህዴድ ባለስልጣናት አድማው እንዳይካሄድ ለማድረግ ወደ አካባቢው አቅንተው ነበር።
በሌላ በኩል ነጋዴዎች ለመብታቸው እንዲነሱ የሚያሳስቡ የጥሪ ወረቀቶች በይርጋለም ከተማ በግድግዳዎችና በመብራት ምሰሶዎች ላይ ተለጥፈው መታየታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። “ ለአልመረጥነው መንግስት ግብር አንገብርም፣ በዘፈቀደ የሚጫንብንን ግብር አንከፍልም፣ ይህ የግብር ጫና ነጋዴውን ብቻ ሳይሆን ሸማቹንም የሚጎዳ በመሆኑ በጋራ እንነሳ” የሚሉና ሌሎችም መልዕክቶች ተላልፈዋል።
በዚህ ሳምንት በሃዋሳ እና አርባምንጭ ከተሞችም ተመሳሳይ የጥሪ ወረቀቶች ተበትነው ነበር።