ደም አፋሳሽ ሆኖ የቀጠለውን የጉጂ ዞን ግጭት የአካባቢው ባለስልጣናት እንዳስነሱት ነዋሪዎች ተናገሩ

ሐምሌ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፉት 5 ቀናት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና እስከ 1 ሺ የሚጠጉ ቤቶች መቃጠላቸውን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭቱን የጉጂ ዞን ባለስልጣናት እንዳስነሱት ይገልጻሉ። ኢሳት በተከታታይ ያቀረባቸው ዜናዎች የአንድን ወገን መረጃ ብቻ ማእከል ያደረገ ነው በማለት ቅሬታቸውንም አቅርበዋል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት ግጭቱ የጉጂ ዞን ባለስልጣናት በደቡብ ክልል ስር የሚገኙ የኮሬ ማህበረሰብ አባላትን ለማጥቃት ሆን ብለው የቀሰቀሱት ነው።
የኮሬ ማህበረሰብ አባላት በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የጉጂ ዞን ባለስልጣናት በደንብ የታጠቁና የሰለጠኑ የኦሮምያ ልዩ ሃይል አባላትን በማሰማራት ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል። የኮሬ ማህበረሰብ አባላትም ራሳቸውን ለመከላከል እንዳልቻሉና ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ግጭቱ በደንብ በታጠቀ እና በተደራጀ መልኩ በዞን አስተዳዳሪዎች መሪነት የሚካሄድ መሆኑን የሚናገሩት የኮሬ ብሄረሰብ አባላት፣ በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አካባቢያቸውን በመልቀቅ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተሰደዱ ነው።
ከሁለቱም ወገኖች እስካሁን ከ13 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ቢገለጽም፣ ቁጥሩ ግን ከዚህ የሚበልጥ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በመጀሪያው ቀን ላይ መሳታፋቸውን ኢሳት መግለጹ ይታወቃል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላ አገሪቱ የሚታየው የጎሳ ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ እየደረሰበት ያለውን ፖለቲካዊ ተቃውሞ ለማብረድ በህዝቡ መካከል ግጭት እየፈጠረ፣ ህዝቡ በአንድነት ተባብሮ እንዳይነሳ የማድረግ ስትራቴጂ እየተከተለ ነው በማለት ተቃዋሚዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።