ሐምሌ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህወሃት ውስጥ በመከላከያና በደህንነት ሃይሉ መካከል የተነሳውን የቆየ ልዩነት ተከትሎ የደህንነት ሃይሉ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በመከላከያ ውስጥ የተፈጸመውን ሙስና በማጣራት፣ የተወሰኑ ቡድኖችን ለመምታት የተደረገው ሙከራ ፣ ምርምራው እንዲታፈን መደረጉን ምንጮች ገለጹ። መረጃ የሰጡ የተለያዩ ሰዎች መታሰራቸውንም ለማወቅ ተችሎአል።
በጄ/ል ሳሞራ የኑስ የሚመራው መከላከያና በጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ፣ የጌታቸው አሰፋ መስሪያ ቤት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን፣ ከጄ/ል ሳሞራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በሙስና ለመክሰስና ለማስወገድ ለወራት ምርምራ ሲያድርግ ቢቆይም፣ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ መረጃዎች ታፍነው እንዲቀሩና መረጃ የሰጡ ሰዎች እየተለቀሙ እንዲታሰሩ መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል። መረጃ አቀብላችሁዋል ተብለው ከታሰሩት መካከል ወታደራዊ መኮንኖችና የደህንነት አበላትም ይገኙበታል።
በመከላከያ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምርምራ መደረጉን እንደሰሙ በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ሰራተኞች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
ምንጭ እንደሚሉት የደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ በሙስና ስም የተወሰኑ ወታደራዊ አዛዦችን በመምታት ስልጣኑን ለማጠናከር ያደረገው ሙከራ ሳይጨናገፍበት አልቀረም። ምርመራው በሂደት ላይ እያለ፣ የምርምራው ኢላማ ሆነዋል የተባሉ በየ ክልሉ የነበሩ ወታደራዊ አዛዦች ወደ ማእከል እየተጠሩ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ተቀምጠዋል።
የህወሃት ጄኔራሎች በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዘመናዊ ህንጻዎችን ሰርተው እንደሚያከራዩ ይታወቃል።