ከእለታዊ ግብር ጋር በተያያዘ የተጀመረው የነጋዴዎች አድማ በምስራቅ ጎጃምና በምስራቅ ሃረርጌ ቀጥሎ ዋለ

ሐምሌ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ገቢያችንንና ኑሮአችንን ያላገናዘበ የግምት ግብር ይቀየርልን በማለት ተቃውሞ ያሰሙ ነጋዴዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ላለፉት 2 ሳምንት ድርጅቶቻቸውን በመዝጋት ሲያደርጉ የነበረውን አድማ ዛሬም ቀጥለዋል። ለተከታታይ አምስት ቀናት አድማውን እያደረጉ ካሉት ከተሞች መካከል የምስራቅ ጎጃሟ ሞጣ አንዷ ስትሆን፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ጉልበትን ጨምሮ የተለያዩ ማስፈፋሪያዎችን ተግባራዊ ቢያደርጉም ነጋዴዎች ግን ለማስፈራሪያው የሚበገሩ አልሆኑም።
በከተማዋ ያሉት የንግድ ድርጅቶች በሙሉ ተዘግተዋል። የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ናቸው የሚባሉ የንግድ ድርጅቶች ድርጅቶቻቸውን ለመክፈት ሲሞክሩ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።
የምስራቅ ጎጃም ከተሞች የሆኑት ሸበል በረንታ፣ የደውሃ፣ ደጀን ቢቸና፣ ጉንድወይን ጠንካራ አድማ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
በምስራቅ ሃረርጌ ደደር ወረዳ የተነሳውን የነጋዴዎች አድማ ለመቆጣጠር የኦህዴድ ባለስልጣናት በብዛት መሰማራታቸው ታውቋል። የተለያዩ የአድማ የጥሪ ወረቀቶችም እየተበተኑ ነው።