ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላ አገሪቱ ላለፉት 2 ሳምንታት የተካሄደው የንግዱ ማህበረሰብ አድማ ዛሬም ቀጥሎአል። በአዲስ አበባ በአየር ጤና አካባቢ የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ መደብሮችን በመዝጋት ተቃውሞ እያደረጉ ሲሆን፣ አካባቢው በፖሊሶች ተወሯል። በደጀን ከተማም እንዲሁ ትናንት የተጠራውን አድማ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ዛሬ ተግባራዊ አድርገውታል።
ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ጭር ብላ የዋለች ሲሆን፣ ነጋዴዎች ያለአገባብ የተጣለባቸው የቀን ገቢ ግብር እንዲቀርላቸው ካልሆነ ግን በአድማው እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።
በአዋሳና አርባምንጭ ደግሞ ሌሊቱን እና ቀን ላይ በርካታ የጥሪ ወረቀቶች ተበትነዋል። የጥሪ ወረቀቶች ነጋዴዎች የእለታዊ ግብርን በመቃወም አድማ እንዲያድረጉ የሚያሳስብ ነው።
በአርባምንጭ ዛሬ በተከበረው የገብርኤል በአል ላይ ሳይቀር የተቃውሞ ወረቀቶች ሲሰራጩ መዋላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ታሪካዊ የተባለውን አድማ መጀመራቸውን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የአገዛዙ ባለስልጣናት የግብር ቅናሽ መደረጉን በመግለጽ ነጋዴዎች አድማውን እንዲተው ለማግባባት እየሞከሩ ነው። በተለይ በምስራቅ ጎጃም የሚገኙ ባለስልጣናት ቤት ለቤት እየዞሩ ግብር አምሳ በመቶ ተቀንሷል እና ድርጅቶቻችሁን ክፈቱ በማለት ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።