ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና አለመታሰራቸው ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 19/2009)በሀገር ቤት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት በሙስና ተጠርጥረው ታስረዋል ከተባሉት 34 ባለስልጣናት፣ነጋዴዎችና ደላሎች መካከል የተንዳሆና መተሃራ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ሃላፊዎች ተጠቃሽ ሆነዋል።

ሰንደቅ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ሃላፊዎች ስራ አስኪያጁ አቶ አበበ ተስፋዬ፣የፋይናንስ ዘርፍ ስራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ድምጹ፣እንዲሁም የንብረት አስተዳደር ዳይሬክተሩ አቶ በሃይሉ ገበየሁ፣የፋብሪካው የቀድሞ የግዢና ንብረት አስተዳደር ሃላፊው አቶ ኤፍሬም አለማየሁ ከታሳሪዎቹ መካከል ይገኙበታል።

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ የግዢ ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፣እንዲሁም በዚሁ ፋብሪካ በተለያየ የሃላፊነት ዘርፍ ላይ የነበሩት ወይዘሮ ሰናይት ወርቁና አቶ ሃየሎም ከበደ መታሰራቸውም በዘገባው ተመልክቷል።

በአጠቃላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መታሰራቸው በመንግስት ሀላፊዎችና መገናኛ ብዙሃን ቢገለጽም የታሰሩት በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ የፋብሪካ ባለስልጣናት ያውም በአብዛኛው የቀድሞ ሃላፊዎች መሆናቸውን ከዘገባዎችና ከምንጮቻችን መረዳት ተችሏል።

ከእስራቱ ጋር በተያያዘ በሚኒስትር ደረጃ የታሰረ አንድ ግለሰብ መኖሩ ቢገለጽም እሱም የቀድሞ ሚኒስትር እንደሆነም መረጃው አመልክቷል።የግለሰቡን ማንነት ግን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ከ6 ወር በፊት ከ130 በላይ ሃላፊዎች መታሰራቸውና ንብረታቸው መታገዱ ቢገለጽም በተጨባጭ የታሰረ ሰው እንዳልነበር ተረጋግጧል።

በወቅቱ ሁለት ሚኒስትሮች መታሰራቸው ቢገለጽም ወዲያው መለቀቃቸው ተመልክቷል።