ኢሳት ዜና (ሀምሌ 4 ,2009 )በኢትዮጵያ የአበባ ኢንቨስትመንት በመሬት አቅርቦት እጥረት መገታቱን ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለፓርላማ ገለጹ ።
በኢህአዴግ ፓርላማ የ2010 በጀትን ለማጽደቅ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪኣም ደሳለኝ የሃገሪቱ የውጪ ንግድ እያሽቆለቆለ መሆኑን ተናግረዋል ። ችግሩን እንዲጎላ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል በአበባ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ምክንያት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ፌደራል መንግስት ያረገው ጥረት የክልል መስተዳደሮች መሬት አናቀርብም በማለታቸው ተስተጓጉሏል ሲሉ ስሞታ አቅርበዋል ።
አቶ ሃይለማሪያም በገለጻቸው ለአበባ እርሻ የሚሆን መሬት ባለመገኘቱ ፌደራል መንግስት በአማራጭ መፍትሄነት ከመንግስት ልማት ድርጅት ይዞታዎች ውስጥ የሚገኙ መሬቶችን ለመጠቀም እየተገደደ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው የውጪ ንግድ እያሽቆለቆለ መሆኑ የሃገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት እያባባሰው መምጣቱን የአለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት መግለጹ የሚታወስ ነው ። ላለፉት አስር አመታት በሃገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መካከል የታየው የንግድ ሚዛን ጉድለት በአማካይ 50 ቢሊዮን ብር ነበር ።በተለይ ባለፈው አመት የነበረው የንግድ ሚዛን ጉድለት ከ87 ቢሊዮን ብር በላይ ማሻቀቡን የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርቶች ይጠቁማሉ ።
በኢትዮጵያ የአበባ ኢንቨስትመንት በአንድ ወቅት ሰሞንኛ አጀንዳ ሆኖ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሽፋን ሲያገኝ እንደነበረ አይዘነጋም ።በአበባ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እየተገኘ እንደሆነ ሲገለጽ ቢቆይም በኋላ ላይ ግን ምርቱን የሚወስዱ ሃገሮች ፊታቸውን በማዞራቸው ባለሃብቶቹ ማማረር መጀመራቸው ይታወሳል ።
ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የውጪ ዜጎች ሲሳተፉበት የቆዩት የአበባ ኢንቨስትመንት ጎጂ ኬሚካሎችን ስለሚጠቀም በሰራተኛ ላይ ጉዳት በማድረሱም ተቃውሞ አስነስቶ ነበር ።በኢትዮጵያ ህዝባዊ አመጽ በተቀሰቀሰ ጊዜም የአበባ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም መገለጹ ይታወቃል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም በፓርላማ ቀርበው የአበባ ኢንቨስትመንት የተዳከመው በመሬት እጦት ነው ቢሉም ከዘርፉ ጋር ያሉ ሌሎች በርካታ ችግሮችን ግን አላነሱም ።