ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2009)
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በቀጣዬቹ 80 ዓመታት ኢትዮጵያ ከ60 በመቶ በላይ የቡና ምርቷን ልታጣ እንደምትችል አንድ ጥናት አመለከተ።
ኔቸር ፕላንትስ የተሰኘ የሳይንስ መፅሄት ላይ የወጣው አዲስ ጥናት እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከፍተኛ ወደሆኑ መልከአምድሮች ምርታቸውን ካላበቀሉ 60 በመቶ የቡና ምርት ሊጠፋ ይችላል።
በጥናቱ እንደተገለፀው የአካባቢ የአየር ንብረት ተፅዕኖ የሙቀት መጨመር አነስተኛ የዝናብ መጠን እና ድርቅ የቡና አብቃይ አካባቢዎችን እየጎዳ ይገኛል። የኢትዮጵያ ቡና እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010 ከ39 እስከ 59 በመቶ ሊጠፋ እንደሚችል ጥናቱ አስጠንቅቋል።
ለዚህ የተሰጠው ምክንያት ደግሞ አሁን ቡና የሚያበቅለው አካባቢ የመሬት ሁኔታ በአየር ንብረት ለውጥ ስለሚጎዳ መሆኑን አይ ኤፍ ኤል ሳይንስ የተሰኘ በእንግሊዝ አገር የሚታተም መጽሄት ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የቡና ተክል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበት አካባቢ መሆኑን እና በ10ኛው ክፍለ ዘመን በሀገሪቱ የነበሩ ከብት አርቢ ሰዎች የፍሬውን ጣዕም ማወቃቸውን ዘገባው አስታውሷል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ኮፊ አረቢካ የተባለው የቡና ዝርያ ለዓለም ገበያ በማቅረብ በ5ኛ ደረጃ ትልቁን ሥፍራ የያዘች መሆኗንም ተጠቅሷል።
በአፍሪካ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ በቀዳሚነት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከዚሁ ምርት በዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝም ለማወቅ ተችሏል። በዚሁም 15 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከቡና ምርት ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን እንደሚመሩም ይገልፃል።
አሁን ባለው ሁኔታ የዓለም የሙቀት ሁኔታ ባለፉት 50 ዓመታት ብቻ በአማካይ 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲጨምር የዝናብ መጠኑ ደግሞ በ40 ኢንች ቀንሷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ የቡና ምርት እየቀነሰ መምጣቱን ከወዲሁ ምልክቶች እየታየ መሆኑንም ጥናቱ አመልክቷል።
ገበሬዎች የቡና ተክላቸውን ወደ ደጋና ከፍተኛ ወደሆኑ አካባቢዎች ቢወሰዱ ምርቱን ከጥፋት ለመታደግ እንደሚቻል አጥኝዎቹ መክረዋል።