ከአውስኮድ ክለብ ጋር ባህርዳር ላይ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማድረግ የነበረበት የመቀሌ ቡድን በጸጥታ ምክንያት ጨዋታውን ሰረዘ

ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2009)

ከአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት /አውስ ኮድ / ክለብ ጋር የእግር ኳስ ውድድር ለማካሄድ ባህር ዳር መግባት የነበረበት የመቀሌው ከነማ ቡድን በጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታውን መሰረዙ ተሰማ ። የመቀሌው እግር ኳስ ክለብ ከአማራ ስፖርት ኮሚሽንና ከክልሉ መንግስት የጸጥታ ዋስትና እንዲሰጠው ጠይቆ የጽሁፍ ደብዳቤ ባለማግኘቱ በጸጥታ ስጋት ጨዋታውን መሰረዙ ታውቋል።  

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደራል ህግና ደንብ መሰረት አንድ ክለብ በራሱ ምክንያት ጨዋታውን ከሰረዘ በፎርፌ እንደተሸነፈ ይቆጠራል ። ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምን ሊወስን እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም። የመቀሌው እግር ኳስ ቡድን በራሱ ሜዳ ከባህር ዳሩ የከነማ ክለብ ጋር ባካሄደው ጨዋታ ደጋፊዎቹ ወደ ሜዳ በመግባት የተጋጣሚውን ተጫዋቾች በመደብደባቸውና በመስደባቸው ውድድሩ መቋረጡ ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎም ግጭቱ ተባብሶ የባህርዳር ከነማ ተጫዋቾች ከመቀሌ እንዳይወጡ ከታገቱ በኋላ የመጡበት አውቶብስ ተሰባብሮ ወደ ክልላቸው መመለሳቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

ግጭቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጨዋታው ኮሚሽነር የቀረበውን ሪፓርት ወደ ጎን በመተው የባህርዳር ክለብ ተጫዋቾችን ዋንኛ ጥፋተኛ በማድረግ ክለቡንና የቡድኑን መሪዎች በገንዘብና በጨዋታ መቅጣቱ ይታወቃል። ከውሳኔው በኋላም ግንቦት  29፣  2009 አም የተቋረጠው ጨዋታ ተመልካች በሌለበት በመቀሌ እንዲካሄድ ቢወሰንም እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም። ይህ በእንዲህ እንዳለም የመቀሌው የከነማ ክለብ በነገው ረቡዕ ሰኔ 14 2009 ከባህር ዳሩ አውስ ኮድ ጋር ለመጫወት ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም የመቀሌው ቡድን በጸጥታ ስጋት ውድድሩን ለማካሄድ አለመፈለጉን ገልጿል።

የጨዋታው ዳኞች ግን ከአዲስ አበባ ባህር ዳር መግባታቸውን የኢሳት ምንጮት ገልጸዋል።