ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ከሚታይባቸውና እንደ መንግስት መቀጠል ካቃታቸው መካከል ከቀዳሚዎቹ 15 ሃገራት እንዷ መሆኗ አንድ አለም አቀፍ ጥናት አመለከተ።
መቀመጫውን በዚሁ በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገውና ፈንድ ፎር ፒስ የተባለው ተቋም በ2017 ይፋ ባደረገው ጥናት የኢትዮጵያ መንግስት ያለመረጋጋት የሚታይበትና ሃገርን አንድ አድርጎ ለመምራት በማይችልበት አቋም ላይ ይገኛል ብሏል።
በአለም አቀፍ ተቋሙ መመዘኛ መሰረት እንደ መንግስት መቀጠል አለመቻል፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ተገምግመዋል። በአጠቃላይ መመዘኛዎችን ግን እየተፍረከረኩና እንደ መንግስት መቀጠል ያልቻሉ የተባሉት አገራት ግዛትን መቆጣጠር አለመቻል ለዜጎቹ ማህበራዊ አገልግሎት ለመስጠት አለመቻል እና የሙስና መንሰራፋት መመዘኛ ተደርጓል።
የከፍተኛ ወንጀሎች መንሰራፋት የህዝብ መፈናቀልና ስደትም ዋነኛ መለኪያ መሆናቸውንም ተገልጿል። የኢኮኖሚ ውድቀትም ሌላው የመንግስት መፈራረስ ማሳያ መደረጉንም ጥናቱ አመልክቷል። በእነዚህ መለኪያዎች ሃገራት ተገምግመው ኢትዮጵያ ከ178 ሃገራት እንደመንግስት መቀጠል ካልቻሉት 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ፈንድ ፎር ፒስ የተባለው ተቋም አስታውቋል።
የኢትይጵያ እንደ መንግስት አለመቀጠል መለኪያ መስፈርት መሰረትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣጡን ጥናቱ ያመለክታል።
አሁን በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ደርግን ከጣለ በኋላ አንጻራዊ ሰላም ማስፈርኑን ጥናቱ አስታውሶ፣ ይህም ሆኖ ግን በሃገሪቱ በተፈጠረው የዕርስ በርስ የጎሳ ግጭትና እኤአ በ1998 እና 2000 ዓም ጊዜ ውስጥ ከኤርትራ ጋር በተካሄደው ጦርነት የሃገሪቱ ሰላም ወደ ማሽቆልቆል መውረዱን ጠቅሷል። አሁንም ቢሆን ባለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ነው ጥናቱ የጠቆመው።
ባለፉት አመታትም ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን እንደ መንግስት መቀጠል ያቃታቸው ሃገራት በሚል መፈረጇን ጥናቱ አመልክቷል።
በ2007 የነበረው የመንግስት አለመረጋጋት አቋም መለኪያ 6.7 የነበረው አሁን ከ10 አመት በኋላ በዚህ አመት 8.7 ማሻቀቡን መረጃው አመልክቷል። የህዝብ አገልግሎት አሰጣጡ ቀንሶ በፊት ከነበረው የማሽቆልቆሉ ሂደት ተፋጥኗል ተብሏል። ይህም የንጹህ ውሃ አለመኖር፣ የጤና ሽፋን መዳከም አሳይቷል ሲል በአህዝ አስደግፎ አጣቅሷል። በኢትዮጵያ በሃኪም ቁጥጥር የሚወሉዱ ህጻናት 15 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጿል። ለ48 ሺ ሰዎችም አንድ ዶክተር ብቻ እንደሚደርሳቸው ጥናቱ አመልክቷል።
በብሄርና በጎሳ የተደራጀው የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖምውን በወታደራዊ ዕዝ ውስጥ በማስገባት የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርምፖሬሽ እንዲቆጣጠርም ተደርጓል ተብሏል። ይህም ሆኖ ሙስናውና ዘረፋው ከፍተኛ መሆኑን ገሉጻል።
ኢህአዴግ በተሰኘው የፖለቲካ ግንባር የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት (ህወሃት) ትግራይ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጥናቱ የስረዳል። እናም ህወሃት ሁሉንም ነገር በበላይነት ተቆጣጥሮ በመያዙ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት እንደሌለ ፈንድ ፎር ፒስ የተባለው አለም አቀፍ ተቋም ይፋ አድርጓል። በዚሁ ሳቢያ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የህዝብ ተቃውሞ በመነሳቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በጥናቱ ተብራርቷል።