በአማራ ክልል በሚገኙ አጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ ተከስቶ ከ250 በላይ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸው ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2009)

በአማራ ክልል በሶስት ዞኖች ስር በሚገኙ 12 ወረዳዎች የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ ተከስቶ ከ250 በላይ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸው የክልሉ ጤና ቢሮ አረጋገጠ።

በሃሙስ ዘገባችን ምንጮች በዚሁ የበሽታ ወረርሽኝ በትንሹ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የሰጠው ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም።

በሽታው በአሁኑ ወቅት በ 12 ወረዳዎች መከሰቱን የገለጸው የክልሉ ጤና ቢሮ 47 ሰዎች በህክምና ተቋማት ተገኝተው እየታከሙ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ይኸው የበሽታ ስርጭት ካለፈው ወር አጋማሽ ጀመሮ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደርና፣ በምዕራብ ጎጃም ዞኖች 12 ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ 252 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ታውቋል።

የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ተከስቶ ለ780 አካባቢ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት (WHO) በቅርቡ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

ሰዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህልፈተ-ህይወት እንደሚዳርግ የሚነገርለት አተት በተለይ ከውሃ ንጽህና እጥረት ጋር በተገናኘ እንደሚከሰት የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋርና የሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከምግብ እጥረት በተጨማሪ በውሃ ወለድ ተላላፊ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን ሲገልፅ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅትም በሶማሌ ክልል ስር ከ700 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የበሽታው ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ያልዋለ ሲሆን፣ ከ 30 ሺ በላይ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውን ከአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በሽታው ጉዳትን እያደረሰ እንደሆነ ቢያረጋግጥም፣ ከበሽታው ስርጭት ጋር በተገናኘ የሞተ ሰው ይኑር አይኑር የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

ይሁንና የአካባቢው ነዋሪዎች የበሽታ ስርጭቱ በክልሉ ባለስልጣናት ከሚገለጸው በላይ ችግሩን እያደረሰ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተክለሃይማኖት ገብረህይወት በተያዘው በጀት አመት የበሽታው ስርጭቱ በክልሉ ለሶስተኛ ጊዜ መከሰቱን አስታውቀዋል።

ይሁንና ሃላፊው ከዚህ በፊት የበሽታው ስርጭት ስላደረሰው ጉዳት የሰጡት መረጃ የሌለ ሲሆን፣ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰው አተት ወደ አጎራባች ወረዳዎች ይዛመታል የሚል ስጋት አሳድሯል።

አለም አቀፍ የህክምና ባለሙያዎች የኢትዮጵያ መንግስት የወረርሽን በሽታን ይደብቃል ሲሉ በቅርቡ ትችት ማቅረባቸው ይታወሳል። ከዚህ በፊት በክልሉ ተከስቶ በነበረው የበሽታው ወረርሽኝ 60 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸው እንደነበርም አይዘነጋም።