በጋምቤላ ክልል በጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ከሁለት ሺ በላይ ነዋሪዎች ዕርዳታ እንዳልደረሳቸው ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2009)

በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ደርሶ በነበረ የጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ከሁለት ሺ በላይ ነዋሪዎች አሁንም ድረስ ዕርዳታን አየተጠባበቁ እንደሆነ ተገለጸ።

በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በክልሉ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 2ሺ 400 አካባቢ ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ አስታውቋል። ይሁንና ነዋሪዎቹ ከመኖሪያ ቀያቸው ከተፈናቀሉ አንድ ወር አካባቢ ቢሞላቸውም አሁንም ድረስ እርዳታን በበቂ ሁኔታ እንዳላገኙ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።

በቅርቡ የነዋሪዎቹን ሁኔታ ለማወቅ በተካሄደ ዳሰሳ 2ሺ 400 የሚደርሱት የአምስቱ ቀበሌዎች ነዋሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ መረጋገጡን ድርጅቱ አመልክቷል።

ነዋሪዎቹ ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ በጎርፉ አደጋ ያጡ ሲሆን፣ ወደ 950 አካባቢ የሚጠጉ ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁሳቸው በመውደሙ ምክንያት ትምህርታቸው መስተጓጎሉ ታውቋል።

የጋምቤላ ክልል የእርዳታ መከላከልና ማስተባበሪያ ቢሮ ነዋሪዎቹ ለሶስት ወራት የሚያገለግል የምግብ ድጋፍ እና የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንደሚፈልጉ ገልጿል።

በክልሉ በጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው ከተፈናቀሉት ነዋሪዎች በተጨማሪ ከወራት በፊት ከደቡብ ሱዳን የሰረጉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ሲገለጽ ቆይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የተጋለጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት በምግብ እጥረቱ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው ያለ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን አስታውቋል።

በደቡባዊ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ዞኖች በምግብ አቅርቦቱ ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን፣ ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በወቅቱ አለመገኘት ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ለተረጂዎች እያቀረበ ያለው የምግብ እርዳታ ሙሉ ለሙሉ ሊያልቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ በማሳሰብ ላይ ነው።

ጉዳትን እያደረሰ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ አለም አቀፍ ትኩረትን እንዲያገኝ በማሰብ የአለም አቀፍ የጋዜጠኞች ቡድን፣ የገልፍ ሃገራት እና፣ የእርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች ከሃሙስ ጀምሮ ለሶስት ቀን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ገልጿል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት በዚሁ የአለም አቀፍ ጉብኝት ፕሮግራም ለድርቁ ድጋፍ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ዕቅድ መኖሩ ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት 7.8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ የተረጂዎቹ ቁጥር ያሻቅባል ተብሎ ይጠበቃል።