የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ከ 20 ቢሊዮን ብር በላይ ከህግ አግባብ ውጭ ማባከናቸው ታወቀ

ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2009)

የጠቅላይ ኦዲት ጽ/ቤት በ158 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ወደ 20 ቢሊዮን ብር አካባቢ ከህግ አግባብ ውጭ መባከኑን አስታወቀ።

የባለፈው አመት በጀት አጠቃቀም አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ሪፖርት ያቀረበው ጽ/ቤቱ፣ በተገባደደው በጀት አመት የተመዘገባው የገንዘብ መባከን ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት እጅ እጥፍ መብለጡንም ገልጿል።

አላስፈላጊ የተባሉ ወጪዎችን ከመጠን ያለፈ በጀት፣ ያልተሰበበሰቡ ግብሮችን፣ እንዲሁም የገባበት ያልታወቀ ገንዘብ መጨመር በበጀት አጠቃቀሙ የታዩ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ገመቹ ዱቢሳ አስረድተዋል።

በበጀት አጠቃቀም ከተመዘገባው የገንዘብ መጠን መጨመር በተጨማሪ የበጀት ግድፈት የታየባቸው መስሪያ ቤቶች ቁጥር ከ37 ወደ 53 መድረሱንም አቶ ገመቹ በሪፖርታቸው መግለጻቸውን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

አብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት ገንዘብ አለአግባብ ጥቅም ላይ የዋለበትን ሁኔታ ለማስረዳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።

ችግሩ ከአመት አመት እየተባባሰ ነው ያሉት አቶ ገመቹ ተጠያቂነት አለመኖሩ ለችግሩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን አስታውቀዋል።

3.7 ቢሊዮን ብር የበጀት ክፍተት የታየባቸው የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፓርላማው ሰፊ ክርክር የተካሄደባቸው ሲሆን፣ 27 ዩኒቨርስቲዎች ችግሩ በስፋት የታየባቸው ሆነው ተለይተዋል።

በዩኒቨርስቲዎቹ የተመዘገበው የበጀት ክፍተት ባለፈው አመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሮ መገኘቱንም ለመረዳት ተችሏል።

“ችግሩን ለመቅረፍ ምንም የተወሰደ ዕርምጃ ባለመኖሩ የገንዘብ ብክነቱና ጉድለቱ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው” ሲሉ የኦዲት ጀኔራል ጽ/ቤት አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 1.2 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት በማስመዝገብ በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋከልቲ እንዲሁም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እያንዳንዳቸው የ472 እና የ 126 ሚሊዮን ብር በጀት ክፍተተ ተገኝቶባቸዋል።

ዩኒቨርስቲዎች ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ፈቃደኛ አይደሉም “በማለት አቶ ገመቹ በበጀት አጠቃቀም ላይ ያለውን ችግር በተመለከተ ለፓርላማ ገልጸዋል።

ህግ ተላልፈው የተገኙ አካላት ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል ሲል አቶ ገመቹ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።

አንዳንድ የፓርላማ አባላት በበኩላቸው ጽ/ቤቱ በየአመቱ ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቃቸው ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በውይይቱ አንስተዋል።