ግንቦት ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር በምትገኘው ጎዴ ከተማ የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት አባል የሆነው የጎንደር ተወላጅ ወታደር በርካታ መኮንኖችን ገድሎ በመጨረሻም ራሱን አጥፍቷል።
ወታደሩ ድርጊቱን የፈጸመው በአየር ሃይል የምህንድስና ትምህርት ተምሮ ጎዴ በእግረኛ ወታደርነት መመደቡን ተከትሎ ነው። ምንጮች እንደገለጹት ፣ ወታደሩ ያለምንም ምክንያት ወደ ጎዴ ተወስዶ በእግረኛ ወታደር አባልነት እንዲሰራ የተመደበ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔም ሲቃወም ቆይቷል። “ ከአየር ሃይል ምድቡ ተነስቶ ለምን በእግረኛ ወታደርነት እንዲሰራ እንደተመደበ መልስ እንዲሰጠው ባለስልጣኖችን በተደጋጋሚ ጠይቆ ምንም መልስ ያላገኘው ወታደር፣ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ጊዜ ሲጠብቅ እንደነበር ምንጮች ይገልጻሉ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የጦር መኮንኖች ከስብሰባ ሲወጡ ጠብቆና አዘናግቶ እርምጃ መውሰዱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ከ10 በላይ የጦር መኮንኖች ተገድለዋል ብለዋል። አካባቢው ወዲያውኑ በመዘጋጋቱ ትክክለኛውን የሟቾችን አሃዝ ለማወቅ ባይቻልም፣ የአካባቢው ምንጮች የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና ፣ ወታደሩም ራሱን ማጥፋቱን ገልጸዋል። ሌሎች ምንጮች ግን ወታደሩ በጠባቂ ወታደር መገደሉንና ራሱን አለማጥፋቱን ይገልጻሉ።
የወታደሩና የመኮንኖቹ አስከሬን እዛው ጎዴ ውስጥ መቀበሩንም ምንጮች ገልጸዋል።
ወታደሩ በቅርቡ በአማራና በኦሮምያ ከነበረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተገምግሞ ወደ ጎዴ በቅጣት መልክ መወሰዱም ታውቋል።
በሌላ በኩል የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ጄ/ል አብረሃ ወደ አዲስ አበባ የተወሰዱት ከሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር የፈጠሩት የጥቅም ግንኙነትን ተከትሎ ገምገማ በመደረጉ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ኢሳት ትናንት ባቀረበው ዘገባ ጄኔራሉ የወታደራዊ ዘመቻ ማስተባባሪያ ውስጥ መመደባቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ቦታው የጀኔራሉን ሹመት ሳይሆን ውድቀት የሚያመለክት ነው በማለት ምንጮች ዘገባውን አርመዋል። ጄ/ል አብረሃ በአሁኑ ሰአት ይህ ነው በማይባል ሃላፊነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ እርሱ በሰራው የሙስና ወንጀል ልክ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ቢሰሩት ኖሮ፣ ሰበብ ተፈልጎ ከስልጣን መባረር ብቻ ሳይሆን ክስ ይመሰረትባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የጄ/ል አብረሃ ምክትል ሆነው ሲሰሩ የነበሩት የኦህዴድ አባሉ ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው ጉዲናም እንዲሁ ከምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥነት ቦታቸው እንዲነሱ የተደረጉ ሲሆን፣ እሳቸውም ስልካቸው ላይ የኦህዴድ ባለስልጣናት ስልክ መገኘቱንና በኦሮምያ በተካሄደው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎ አድርገዋል የሚል ሂስ ተሰንዝሮባቸዋል። ጄኔራሉ የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል። እርሳቸውን ከሃረር በማንሳት ወደ ሌላ ቦታ መመደባቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል በባህርዳር የሚገኙ አንዳንድ የመከላከያ አባላት ፣”ህዝቡ እኛን እንደሰው አያየንም “ ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል። ወታደሮቹ ይህን አስተያየት የሰጡት፣ የግንቦት20ን በአል በማስመልከት ለወታደሮችና አዛዦች በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ነው።
ወኪሎቻችን በድምጽ ቀርጸው በላኩት ማስረጃ ላይ አንድ ወታደር “ በግንቦት 20 በአል ወታደሩ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል ተብሎ ተነግሮናል፣ ነገር ግን ሲቪል ማህበረሰቡ ለወታደሩ ያለው አመለካከት የወረደ ነው።” የሚለው ወታደሩ፣ እኔ እዚህ ከተማ ላይ ያጋጠመኝ ልንገራችሁ ካለ በሁዋላ፣ “ አንድ ቦታ ላይ ሰው ተጣልቶ ስሄድ፣ አንዱ ‘ ሰውና ወታደር ተጣልቶ ነው’ ሲል ሰማሁት። ህዝቡ ለወታደሩ ያለው አመለካከት የዚህን ያክል ነው” ብሎአል።
“የአምበሳውን ድርሻ ይዟል ካላችሁ ፣ ህዝቡ ስለኛ ያለውን አመለካከት እንዲቀይር የሚያደርግ ስራ ስሩ” ሲሉ ስብሰባውን ለሚመሩት ካድሬዎች ተናግሯል ።
ሌላው አስተያየት ሰጪ መኮንን ደግሞ “ ባለፉት 2 እና 3 አመታት ብሄራዊ መግባባታን በተመለከተ እየቀነሰ መጥቷል። በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች እየታዩ ነው። አሁን ብሄራዊ መግባባት በምን ሁኔታ እንዳለ ቢነገረኝ” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ሌላው ወታደር ደግሞ መልካም አስተዳደር የሚባለው ነገር የለም ይላል። “ሙስናን በተመለከተም አንድ ሰው የሙስናን ጉዳይ ሲያጋልጥ የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድበት ምን ዋስትና አለ? እኔ የማውቀው አንድ በሙስና የተዘፈቀ ሰው፣ ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሾም” ገልጾ፣ ሰዎች ሙስናን ሲያጋልጡ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል ብሎአል።
ስብሰባውን የመሩት ኮሎኔል ምንም እንኳ የመከላከያ አባላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ነው ቢባልም፣ እርሳቸው ግን ራሳቸውን የኢህአዴግ አባል አድርገው ድርጅታቸውና መንግስት ሙስናን ለመዋጋት የወሰደውን እርምጃ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ።