ግንቦት ፲፭ ( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ለአገር ውስጥ የሚዲያ አካላት እንደተናገሩት፣ ህወሃት በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ነድፌያለሁ ማለቱ ፣ በአገር ውስጥ የገባበትን የፖለቲካ አጣብቂኝ ተከትሎ ትኩረት ለማስቀየስ በሚል የሚለቀው ፕሮፓጋንዳ ነው። ይህ ትርጉም የለሽ ፕሮፓጋንዳ በኤርትራ ላይ የሚያመጣው ተጽኖ አይኖርም ሲሉም አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል።
ህወሃት የተከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፣ መንግስታቸው ከአካባቢው አገራት ጋር በተለይም ከግብጽ ጋር የጀመረው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኤርትራና ግብጽ በአባይ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የጀመሩት መቀራረብ ነው በሚል ከኢትዮጵያ በኩል የሚቀርበውን ክስ ፕሬዚዳንቱ ጤናማ ካልሆነ አእምሮ የሚመነጭ ባዶ ውሸት ነው ብለዋል።
ምንም እንኳ አቶ ኢሳያስ የፖሊሲ ለውጡ ባዶ ፕሮፓጋንዳ ነው በማለት ቢያጣጥሉትም፣ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎችን እየገዛና ሰራዊቱን እያንቀሳቀሰ ነው። እስካሁን የተሳካ ውጤት ባያገኝም አዲስ የውትድርና ምልመላ ማስታወቂያም በየቦታው ለጥፏል።
ገዢው ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው ተቃውሞ ጀርባ የኤርትራ እጅ አለበት በማለት በተደጋጋሚ ክስ ያሰማል።