ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም የጤና ድርጅት መሪ ሆነው ተመረጡ

ግንቦት ፲፭ ( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአለም የጤና ድርጅትን በዳይሬክተርነት ለመምራት ለመጨረሻው ዙር ውድድር የቀረቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ከኢትዮጵያ ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ ከእንግሊዝ እንዲሁም ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ከፓኪስታን የመጨረሻውን የምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ ካደሩ በሁዋላ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተመርጠዋል።
ሁሉም ተወዳዳሪዎች የ15 ደቂቃ ንግግሮችን ያደረጉ ሲሆን፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቢመረጡ ሁሉም ዜጎች የጤና ሽፋን እንዲያገኙ እንዲሁም አገሮች የራሳቸውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንደሚሰሩ የተናገሩ ሲሆን፣ በተለይ አፍሪካውያንና የደሃ አገሮች እንዲመርጡዋቸው ጠይቀዋል።
ሌላው ተናጋሪ እንግሊዛዊው ዴቪድ ንባሮ ሲሆኑ፣ እርሳቸው ደግሞ የ40 አመት ከስራ ጋር በተያያዘ ያገኙትን ልምድ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መስራታቸውን በማንሳት፣ የጤና ድርጀቱን ወቅቱ በሚፈልገው መጠን ለመቀየር እንደሚችሉ በመናገር ምረጡኝ ብለዋል።
ፓኪስታናዊዋ ዶ/ር ሳኒያ ንሽታርም እንዲሁም ከደሃ አገር የመጡ መሆናቸውን በማጉላትና በህይወት ዘመናቸው ያገኙዋቸውን ድሎች በመዘርዘር ቢመረጡ ድርጅቱን ቀልጠፋና ለችግሮች ፈጥኖ ደራሽ እንደሚያደርጉት ቃል ገብተዋል።
ከሶስቱ እጩ ተወዳዳሪዎች ከአገራቸው ዜጎች ብቸኛ ተቃውሞ የቀረበባቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ናቸው። ኢትዮጵያውያን የዶ/ር ቴዎድሮስ መመረጥ አጥብቀው የሚቃወሙት “ባለስልጣናት በህዝባቸው ላይ ለሚፈጽሙት ወንጀል አለማቀፍ ድርጅቶችን መሸሸጊያ እንዳያደርጉ ለማድረግ ነው “ በማለት ሲከራከሩ ሰንብተዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ና የጤና ጥብቃ ሚኒስቴር ሆነው ሰርተዋል። በሁለቱም ሚኒስቴሮች የተለያዩ በወንጀል የሚያስጠይቁዋቸውን ውሳኔዎች ማሳለፋቸውን አርበኞች ግንቦት 7 መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ሰሞኑን በዝርዝር አቅርቧል።
በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጀኔቭ ተገኝተው ዶ/ር ቴዎድሮስን በጽኑ ተቃውመዋል። ታዋቂው አክቲቭስት አቶ ዘላለም ተሰማም እንዲሁ በጉባኤው ላይ ተገኝቶ ድምጹን ከፍ አድርጎ በማሰማት ተቃውሞውን አሰምቷል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የታየውን የኮሌራ በሽታ መደበቃቸውን ተዋቂዎቹ ዋሽንግተን ፖስትና ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግበዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ በርካታ አገራትን የያዘውን የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ በማግኘታቸው ሊያሸንፉ ችለዋል።