ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2009)
የብሪታኒያ መንግስት ባለስልጣናት በሃገሪቱ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ በሚመከረው አለም አቀፍ ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ የኢትዮጵያ መሪዎች ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ ዙሪያ እንዲመክሩ የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሃሙስ ጥሪ አቀረበ።
በለንደን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በዚሁ ጉባዔ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተሳታፊ ሲሆኑ ከብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቴሬሳ ሜይ ጋር ውይይትን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን ወክሎ የሚገኘውና የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሪፕሪቭ የብሪታኒያ መንግስት በዚሁ ውይይት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በሚለቀቁበት ጉዳይ ዙሪያ እንዲመክሩ አሳሰቧል።
የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት የሃገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሚፈቱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በቂ ጥረት እያደረገ አይደለም ሲሉ ባለፈው ወር ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል።
የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ፊርማ በማሰባሰብ መንግስት ዕርምጃ እንዲወስድ ዘመቻ መክፈታቸውም አይዘነጋም።
በሪፕሪቭ ተቋም ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሃሪት ማክ-ኩሎች የብሪታኒያ መንግስት ለዜጋው መብት መከበር ቅድሚያን በመስጠት በለንደን ከሚገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣን ጋር የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲመክሩ አሳስበዋል።
በለንደን በመካሄድ ላይ ባለው የሶማሊያ አለም አቀፍ ጉባዔ የኢትዮጵያና የተለያዩ ሃገራት ተወካዮች ተሳታፊ ሲሆኑ ሃገሪቱ ሰላሟን በምታገኝበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ እንደሚገኝ ታውቋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በብሪታኒያ መንግስት አስተባበሪነት በተዘጋጀው በዚሁ አለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ሶማሊያ በቀጣዮቹ ሶስት አመታት ውስጥ አስተማማኝ እንድታገኝ ሰፊ ውይይት እየተካሄድ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ሃይልን አሰማርተው የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ተወካዮች በለንደኑ ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ጨምሮ የዩጋንዳ፣ የኬንያ፣ የማላዊ፣ የብሩንዲና የጅቡቲ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን ከ22 ሺ የሚበልጡ ሰላም አስከባሪዎች ሰላምን ለማስፈን ጥረት እያደረጉ ይገኛል። ይሁንና የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ሆኖ ይገኛል።