ህዳር 29 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እውቁ የታሪክ ባለሙያ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ኢትዮጵያን ያገለገሉት፣ ከሶስት አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ ፣ የመለስ ፖሊሲ አገሪቱን እንደማይጠቅማትና ለትግራይ ህዝብም አደገኛ መሆኑን ተናግረው እንደነበር፣ ከእርሳቸው ጋር ቅርበት የነበራቸው ሰው ገለጠዋል።
ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉት ምንጫችን እንደተናገሩት፣ ደጃዝማች ዘውዴ ይህን የተናገሩት በዶ/ር ክንፈ አብረሀ ይመራ የነበረውንና አሁን አቶ ስብሀት ነጋ የሚመሩትን የአለማቀፍ የሰላምና የልማት ተቋም እንዲመሩ በአቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄ በቀረበላቸው ጊዜ ነው።
ደጃዝማች ዘውዴ ለእኚሁ ታማኝ ምንጭ እንደገለጡላቸው፣ ሸመቱን እንዲቀበሉ በተጠየቁበት ጊዜ ለአቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄ አቅርበውም ነበር።
ደጃዝማቹ ያቀረቡት ጥያቄ “ለምንድነው የትግራይን ሰው ብቻ የምትሾመው፣ የትግራይ ህዝብ እንደምታውቀው ቁጥሩ በጣም አነስተኛ ነው፣ ይህ ነገርስ ያዘልቃል ብለህ ታስባለህ ወይ ?’ የሚል ሲሆን፣ አቶ መለስም ” አውቃለሁ፣ ነገር ግን የአይሁድን ታሪክ መመልከት አለብዎት። አይሁዶች በባህልና በኢኮኖሚ ጠንካራ በመሆናቸው አለምን ተቆጣጠረዋል። እኔም የትግራይ ተወላጆችን በኢኮኖሚ ጠንካራ በማድረግና ባህላቸውን በማስፋፋት አይሁዶች እንዳደረጉት ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ አደርጋለሁ። የምስራውም ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ነው። እርስዎም ይህን ተቋም እንዲመሩ የተፈለጉት ለዚህ ነው።” በማለት እንደመለሱላቸው ታውቋል።
ደጃዝማች ዘውዴም በአጸፋው ” አይ የአይሁድ ታሪክ የብዙ ሺ አመት የታሪክ ሂደትና በርካታ የታሪክ መስተጋብሮች የፈጠሩት ነው። አንተ በአጭር ጊዜ የአይሁዶችን ታሪክ ይህን ለማሳካት አትችልም፣ የኢትዮጵያም ሁኔታ ከአይሁድ ሁኔታ ጋር ይለያል፣ ሹመቱንም አልቀበልም” በማለት እንደተናገሩ ምንጫችን ገልጠዋል።
ተቋሙን በታማኝነት የሚመራ ሰው በመጥፋቱንም የህወሀት የረጅም ጊዜ ታማኝ ታጋይ ተደርገው የሚቆጠሩት አቶ ስብሀት ነጋ እንደሚሩት ተደርጓል።
አቶ ስብሀት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህወሀትን ታሪክ ከፍ የሚያደርጉ መጽሀፎች በብዛት እንዲታተሙ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደገና እንዲጻፍ ለማድረግ ሰፊ ፕሮጀክት ዘርግተው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።
አጼ ሚኒሊክን የሚያንቋሽሹ መጽሀፍት በህወሀቱ የገዳይ ቡድን መሪ በነበረው ብስራት አማራ በቅርቡ መታተሙ የዚሁ አዲስ ታሪክ የመፍጠር እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው ተብሎአል።
ኢፈርት የሚያካሂደው የኢኮኖሚ ዝርፊያም የኢኮኖሚ የበላይነትን ጠብቆ፣ የፖለቲካውንም ስልጣን ይዞ ለመቆየት ህወሀት የቀየሰው ስልት መሆኑን ምንጫችን አክለው ተናግረዋል።
ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ የሺሬ ገዢ፣ የፍትህ ሚኒሰትር፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ የሶማሊአ አምባሳደር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል።
ከአጼ ዮሀንስ የሚወለዱት ደጃዝማች ዘውዴ ፣ ዮሀንስ አራተኛ የሚል መጽሀፍ ማሳተማቸው ይታወቃል።