ሚያዝያ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሰሜን ጎንደር ወረዳዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች መበራከት ያሰጋው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ ከሱዳን ጋር ‘ የሰው እና የእጽ ዝውውርን መግታት” የሚል ሽፋን በሰጠው ዘመቻ፣ ራስ ምታት ሆነዋል ያላቸውን ታጋዮች የማደን ዘመቻ ጀምሯል።
ኢሳት ቀደም ብሎ እንደዘገበው በሁለቱ ድንበሮች አካባቢ በሚገኙ ጫካዎች ይኖራሉ ተብለው የተጠረጠሩ ታጋዮችን ለማጥቃት የሄዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አቅጣጫ ጠፍቶባቸው ህይወታቸው ሲያልፍ የተወሰኑት ደግሞ ሱዳን ውስጥ ተገኝተዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት በሚል የሱዳን ወታደሮች በአቅጣጫ ጠቋሚነት በአሰሳው እየተሳተፉ ሲሆኑ፣ በእስካሁኑ ዘመቻ ምንም የተጨበጨ ስራ መስራት አለመቻላቸውን የአካባቢው ምንጮች ተናግረዋል።
በአሰሳው ከሁለቱም ወገን በርካታ ወታደሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ወደ ሁለቱ አገራት እየተመላለሱ የሚነግዱ አንዳንድ ነጋዴዎች እየተያዙ ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል።
ሱዳን ከገዢው ፓርቲ ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ታጋዮች ለመውጋት የምታደርገው እንቅስቃሴ፣ የሁዋላ ሁዋላ ዋጋ እንደሚያስከፍላት ታጋዮች በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።